ቢቢሲ ሰራተኞቼን ኢራን እያስፈራራቻቸው ነው ሲል ቅሬታውን ለተመድ አቀረበ

የቢቢሲ ፐርዢያን አገልግሎት

የቢቢሲ ፐርዢያ አገልግሎት ሰራተኞቼ በኢራን መንግሥት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው ሲል ቢቢሲ ቅሬታውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስገብቷል።

የኢራን ደህንነት ወኪሎች በለንደን ተቀማጭ የሆኑ ኢራናውያን የቢቢሲ ጋዜጠኞችን አግተው ወደ ኢራን እንወስዳችኋለን የሚሉ ማስፈራሪያዎች እያደረሱባቸው ነው ብሏል።

ቢቢሲ የሰራተኞቹ ደህንንነት እንዲጠበቅ ሲል እንዲህ አይነት ተማፅኖ ለተመድ ሲያቀርብ የመጀመሪያው አይደለም።

ኢራን ይህንን ውንጀላ ያጣጣለች ሲሆን የቢቢሲ ፐርዢያ አገልግሎት መንግሥትን ለመጣል ሃሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ ነው ብላለች።

የቢቢሲ የህግ ተወካዮች የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በጉዳዩ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

ከኢራን ህዝብ ውስጥ 1/3ኛ የሚሆነው፣ 18 ሚሊዮን ህዝብ ኢራን ላይ የሚያጠነጥነውን የቢቢሲ አገልግሎት በድረ-ገፅ፣ በሬድዮና በሳተላይት ቴሌቪዥን ይከታተላሉ።

በፋርስ ቋንቋ የሚተላለፈው ይህ አገልግሎት በኢራን ውስጥ ታግዷል። ባለስልጣናቱም ከቢቢሲ ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን ኢራናውያንንም በቁጥጥር ስር አውለው ነበር።

ቢቢሲ በ102 ፐርዢያን ሰራተኞቹ ላይ ባደረገው ግምገማ ሰባ አንዶቹ ከኢራን መንግሥት ትንኮሳ እንደደረሰባቸው ነው።

በባለፈው አመት በተደረገው በዚህ ግምገማ ሩብ የሚሆኑት ሰራተኞች በኢራን የሚገኙ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ቤተሰቦቻቸው በኢራን ባለስልጣናት ለጥያቄ ተብለው ተወስደዋል።

በዚህም ምክንያት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሚደርስባቸው ጫና ስራቸውን ለቀው ይወጣሉ።

በያዝነው ሳምንት ሃሙስ ቢቢሲ ከተመድ የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ጎን ለጎን በነዚህ ጋዜጠኞች ላይ በኢራን መንግሥት የሚደርስባቸው ጫናና ትንኮሳን በተመለከተ አንድ ዝግጅት አዘጋጅቶ ነበር።

በዚህም ወቅት የቢቢሲ ሪፖርተር የሆነው ካስራ ናጂ እሱ፣ የስራ ባልደረቦቹም ሆነ ቤተሰቦቹ የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያ፣ ጫናና ሌሎችንም ጉዳዮች በዝርዝር ተናግሯል።

ከዚህም ውስጥ ጫን ያለ እንደ ሞት ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸው አስረድቷል።