በቻይና 'የማርሻል አርት' ማሰልጠኛ ውስጥ የተቀሰቀሰ እሳት ህፃናትን ለሞት ዳረገ

ማርሻል አርት የሚሰለጥኑ ህፃናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ውስጥ 'በማርሻል አርት' ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ 18 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት እንደተዳረጉና 16 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከአደጋው ሰለባዎች ውስጥ የበዛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት መሆናቸውም ተገልጿል።

አብዛኞቹ ተጎጂዎች ከ7 እስከ 16 ዓመት እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ በቻይና ሄነን አውራጃ በሚገኘው ሺንቺንግ 'የማርሻል አርት' ማዕከል ውስጥ እየኖሩ የሚማሩ እንደነበሩም ተመላክቷል።

እሳቱ አርብ ማለዳ ላይ እንደተቀሰቀሰና እንደተዛመተ የአከባቢው ባልሰልጣናት የገለፁ ሲሆን የአደጋው መነሻ እስካሁን አልታወቀም።

የጠበቀ የእሳት አደጋ ቁጥጥር ባላት ቻይና ይህን መሰል አደጋ የተለመደ አይደለም።

የማዕከሉ ሀላፊ የሆነው ግለሰብ ክስተቱን ተከትሎ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአከባቢው አስተዳደር በይፋዊው የ 'ዊ ቻት' ገጹ በኩል ገልጿል።

የእሳት አደጋው በደረሰበት ሰዓት በማዕከሉ 34 አዳሪ ተማሪዎች እንደንደነበሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቻይና ለሚገኝ አንድ የዜና ወኪል ተናግረዋል። ፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በፍጥነት ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ሮይተርስ ያነጋገራቸው ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ ምንም ዓይነት መረጃ እዳላገኙና እንዲጎበኞቸውም እንዳልተፈቀደላቸው ጠቅሰዋል።

"በማዕከሉ ተማሪዎች እየኖሩ በየቀኑ ማርሻል አርት ይማራሉ። ልምምድ ያደርጉ ነበር። የእሳቱ መንስኤ ግን ምን እንደሆነ አላውቅም " ሲሉ ከአደጋው የተረፈ የዘጠኝ ዓመት ልጅ አባት ተናግረዋል።

ሌላ ወላጅ ደግሞ "መረጃዎች በሙሉ ተዳፍኗል" ሲሉ ለሮይተርስ ገልጸዋል፡፡

አደጋው የተፈጠረበት አውራጃ በርካታ ሰዎች ማርሻል አርት የሚሳልጥኑ ተቋማት የሚገኙበት ነው።