የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ስለዩፎዎች ያዘጋጀውን ሪፖርት ይፋ ሊያደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው በዩፎ ወይም ማንነታቸው ባልታወቁ በራሪ ነገሮች ዙሪያ ሲደረግ የነበረው ምርመራ ውጤትን የአሜሪካ መንግሥት በቀናት ውስጥ ይፋ ሊደረግ ነው።
የአገሪቱ መከላከያ ተሽከረካሪዎች በሰማይ ላይ ባልተለመደ መልኩ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ምስል ከመዘገቡ በኋላ ኮንግረሱ ምስጢራዊ ሪፖርቱ ይቅረብልኝ ሲል ጠይቋል።
በኮንግረሱ እና በመከላከያው መካከል የነበረው ግንኙንት ላይ የታየ ከፍተኛ ለውጥ ነው የዚህ ሪፖርት መቅረብ ጉዳይ።
ወታደራዊ መሪዎች እንዳሉት እነዚህ ተንቀሳቃሽ አካላት እንግዳ ፍጥረቶች (ኤሊያን) ካልሆኑ እንደ ሩሲያ ወይም ቻይና ካሉ የአሜሪካ ተቀናቃኝ አገራት የተላኩ ቴክኖሎጂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ባለፈው ነሐሴ ፔንታጎን እነዚህ ያልታወቁ በራሪ አካላትን ጉዳይ የሚመረምር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ነበር።
የቡድኑ ሥራ እነዚህን ክስተቶች "መመርመር፣ መተንተን እና በተለያዩ ቡድኖች መመደብ" እንዲሁም የዩፎዎችን "ተፈጥሮ እና አመጣጥ በተመለከተ ግንዛቤ ማግኘት" ነው ሲል ፔንታጎን ገልጾ ነበር።
ታዲያ በዚህ ወር መጀመሪያ የቡድኑ ሪፖርት ሚስጥራዊ ክፍል ለሕግ አውጪዎች ቀርቧል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት ሪፖርቱ የውጭ የኤሊያኖችን እንቅስቃሴ የተመለከተ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማግኘቱን፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ሃሳቡን ውድቅ የሚያደርግ አድንዳልሆነም ተናግረዋል።
ግብረ ኃይሉ እነዚህ ዩፎዎች ለአሜሪካ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ምስጢር አለመሆናቸውን አረጋግጧል ተብሏል ።
ባለሥልጣኖቹ ባለፈው ዓመት ፔንታገን "ያልታወቁ በራሪ ክስተቶች" ሲል ይፋ ያደረጋቸውን ሦስት ቪዲዮዎችን ጨምሮ ላለፉት 20 ዓመታት የታዩ 120 ተመሳሳይ ክስተቶችን መርምሯል።
ምንም እንኳን ዓለምን የሚያንቀጠቅጥ መረጃ ባይጠበቅም ብዙዎች አጅግ በሚቀልዱበት የዩፎዎች ጉዳይ ላይ መንግሥታዊ ሪፖርት መኖሩ በራሱ ዩፎዎች ከሳይንሳዊ ልብ ወለድነት ወጥተው ወደ አሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ዓለም መግባታቸውን ያሳያል ተብሏል።
በአሜሪካ ሕዝብ መካከል ስለዩፎዎች በርካታጥያቄዎች ሲቀርብ የነበረ ሲሆን ጉዳዩን ከመንግሥት አልፎ ሌሎች ቡድኖችም መመርመርና መጠየቅ ጀምረዋል።
ፔንታገን እጅ የረቀቁ ብዙም ያልታወቁ የአየር ላይ ተንቀሳቃሽ አካላትን መለየት በሚል ፕሮግራሙ ድምጹን አጥፍቶ ከአውሮፓውያኑ 2007 አንስቶ ስለዩፎዎች መረጃዎችን ሲያሰባስብ ነበር።













