በኮሮናቫይረስ ወቅት አምስት ሚሊዮን አዳዲስ ሚሊየነሮች መፈጠራቸው ተገለፀ

ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመላው ዓለም ከአምስት ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲያ ሚሊየነር መሆናቸው ተሰማ።

ብዙዎችን ያደኸየው ይህ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሊየነሮችን ቁጥር ከ5.2 ሚሊዮን ወደ 56.1 ሚሊዮን ማሳደጉን ክሬዲት ስዊስ የተሰኘው የምርምር ተቋም አስታውቋል።

በ2020 በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ አዋቂ ሰዎች ውስጥ አንድ በመቶው ለመጀመሪያ ጊዜ ሚሊየነር የሆነበት ዓመት ነበር።

ለሀታሞቹ የበለጠ ሀብት ማግኘትም የአክሲዮን ገበያ በቶሎ ማገገም እና የቤት ዋጋ መናሩ ምክንያት ሆኗል።

በኮቪድ-19 ወቅት የተፈጠረው ሀብት ወረርሽኙ ካስከተለው የኢኮኖሚ ችግር ጋር "ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም" ሲሉ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና የ'ግሎባል አሴት ሪፖርት' የተባለውን ዘገባ ያዘጋጁት አንቶኒ ሽሮክ በበኩላቸው ወረርሽኙ "በዓለም ገበያዎች ላይ አንገብጋቢ ነገር ግን የአጭር ጊዜ ተፅእኖ" እንዳለው ገልፀው፤ ይህ ግን "በሰኔ ወር 2020 መጨረሻ በጣም ተለውጧል" ብለዋል።

"ዓለም አቀፉ ሀብት በእንዲህ አሰጨናቂ ጊዜ ሳይናጋ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን በእውነቱ በዓመቱ ሁለተኛ አጋማሽ በፍጥነት ጨምሯል" ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2020 በአዋቂዎች መካከል ያለው የሀብት ልዩነት እየሰፋ ሄዷል ያሉት ሾሮክስ እንደ የቤት ዋጋ ጭማሪ ያሉ የቋሚ ንብረቶች ዋጋ ጭማሪዎችን ከትንተናው አውጥተን ከተመለከትናቸው "በዓለም አቀፍ ደረጃ በየቤቱ ያለው ሀብት ወድቆ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

የወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በዓለም ላይ ያለው አጠቃላይ ሀብት በ7.4 በመቶ እድገት አሳይቷል።

ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ10 ሺህ አስከ 100ሺህ ዶላር ያላቸው ሰዎች ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ የጨመረ ሲሆን፤ ይህም በ2000 (እአአ) 507 ሚሊዮን የነበሩት በ2020 አጋማሽ ላይ 1.7 ቢሊዮን ሰዎች ይህን ያህል ገንዘብ አላቸው ማለት ነው።

ለዚህም ምክንያቱ "በማደግ ላይ ያሉ አገራት ሀብት እያፈሩ መሆናቸውና በታዳጊ አገራት ውስጥ የሚገኙ መካከለኛ ገቢያላቸው ሰዎች ቁጥር እያደገ በመሆኑ ነው" ተብሏል።

የክሬዲት ስዊስ ባልደረባ የሆኑት ናኔት ሄሽለር እናዳሉት "በወረርሽኙ ወቅት በመንግሥታት በኩል ግለሰቦችንና የንግድ ተቋማትን ለመደገፍ የተሰጡ ድጋፎችና የወለድ መጠን እንዲቀንስ መደረጉ ከባድ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ እንዳይከሰት አድርጓል" ብለዋል።

ገንዘብ ወደ ኪሱ የሚያስገባ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images