ጆርጅ ፍሎይድን የገደለው የቀድሞው ፖሊስ መኮንን ዴሪክ ቻውቪን ከ 22 ዓመት በላይ እስር ተፈረደበት

ዴሪክ ቻውቪን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዴሪክ ቻውቪን ባለፈው ሚያዝያ በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጥፋተኛ ተብሎ ነበር

ባለፈው ዓመት ግንቦት ሚኒሶታ ውስጥ አፍሪካ አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው አሜሪካዊው ነጭ የቀድሞ የፖሊስ መኮንን 22 ዓመት ከስድስት ወር እስር ተፈረደበት።

የዴሪክ ቻውቪን ቅጣት "የተጣለበትን እምነት እና ኃላፊነት በማጉደል እንዲሁም በታየው ልዩ ጭካኔ" ላይ የተመሠረተ መሆኑን ዳኛው ተናግረዋል።

የ48 ዓመቱ ጆርጅ ፍሎይድ ህይወት ያለፈው ቻውቪን አንገቱ ላይ ለዘጠኝ ደቂቃዎች የህል ተንበርክኮ ተንፋሽ አሳጥቶት ከቆየ በኋላ ነበር።

ግድያው ዘረኝነትን እና የፖሊስ ጭካኔን ሚቃወሙ ዓለም አቀፍ ተቃውሞዎችን አስከትሏል።

የ45 ዓመቱ ቻውቪን ባለፈው ወር በሁለተኛ ደረጃ ግድያ እና በሌሎች ጥፋቶች ተከሶ ነበር። በችሎቱ ወቅት ግድያውን "በቅን ልቦና የተሠራ ስህተት" ሲሉ ጠበቃው ገልጸው ነበር።

በተጨማሪም ቻውቪን እንደ አጥቂ ወንጀለኛ እንዲመዘገብ እና በቀሪ ዕድሜው የጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳይሆን ታግዷል።

ከእሱ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት የቀድሞ መኮንኖች የጆርጅ ፍሎይድን መብቶች በመጣስ በተናጠል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የፍሎይድ ቤተሰቦች እና ደጋፊዎቻቸው ውሳኔውን በደስታ ተቀብለዋል።

ጠበቃው ቤን ክሩም በትዊተር ገጻቸው "ይህ ታሪካዊ ቅጣት ተጠያቂነትን በማስፈን የፍሎይድ ቤተሰቦችን እና አገራችንን ወደ ፈውስ አንድ እርምጃ እንዲጠጉ ያደርጋቸዋል" ብለዋል።

የፍሎይድ እህት ብሪጅት ፍሎይድ ውሳኔው "የፖሊስ ጭካኔዎች በመጨረሻም በደንብ እየታዩ መሆናቸውን ቢያሳይም ገና ብዙ የሚቀር መንገድ አለ" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፍርዱ "ተገቢ ይመስላል" ብለው ዝርዝር ጉዳዮችን እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ውሳኔው ሲሰጥ ምን ተባለ?

የፍርድ ውሳኔው በሚሰጥበት ወቅት የፍሎይድ ወንድም ቴሬንስ ፍሎይድ ከፍተኛው የ40 ዓመት የእስር ቅጣት እንዲወሰን ጠይቋል።

"ለምን? ምን እያሰብክ ነበር? በወንድሜ አንገት ላይ ተንበርክከህ በጉልበትህ ስትጫነው ጭንቅላትህ ውስጥ ምን እየተመላለሰ ነበር?" ሲልም ጠይቋል።

የሰባት ዓመቷ የፍሎይድ ሴት ልጅ ጂያና በቪዲዮ በተቀረጸ መልዕክት አባቷ እንደናፈቃት እና እንደምትወደው ገልጻለች።

"ሁል ጊዜ ስለ እሱ እጠይቃለሁ። አባቴ ሁል ጊዜ ጥርሴን እንዳፀዳ ይረዳኝ ነበር" ብላለች።

ዳኛው ጉዳዩ ለማኅበረሰቡም ሆነ ለአገሪቱ ከምንም በላይ ደግሞ ለፍሎይድ ቤተሰቦች አሳዛኝ ነበር ብለዋል።

ዳኛው ፒተር ካሂል "ፍርዱ በስሜታዊነት ወይም በሐዘኔታ ላይ አልተመሠረተም። በተመሳሳይ ግን ሁሉም ቤተሰቦች በተለይም የፍሎይድ ቤተሰቦች እየተሰማቸው ያለውን ጥልቅ እና ከባድ ህመም አምኜ መቀበል እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ቻውቪን በበኩሉ ለፍሎይድ ቤተሰቦች ሐዘኑን መግለጹን ለፍርድ ቤቱ አስታውቆ "ለወደፊቱ ሌላ መረጃ ይኖራል። ነገሮች ትንሽ የአእምሮ ሰላም ይሰጣቸዋል" ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ሆኖም ግን ለድርጊቱ ይቅርታ አልጠየቀም።

ፍርድ ቤት የተገኙት የቻውቪን እናት "ጥሩ ሰው" እንደሆነ ተናግረዋል።

ካሮሊን ፓውለንቲ "ሁልጊዜም በንጹህነትህ አምናለሁ። ከዚህ ሃሳቤ ስንዝር ፈቀቅ አልልም" ብለዋል ለልጃቸው።

የቻውቪን ቅጣት "የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ላይ እስካሁን ድረስ የተላለፈ በጣም ረዥሙ ቅጣት ነው" ሲሉ የሚኒሶታ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኬት ኤሊሰን ተናግረዋል።