ዩኬ በቀድሞ ባለሥልጣኗ የተመዘበረን 5.8 ሚሊዮን ዶላር ለናይጄሪያ መንግሥት መለሰች

የፎቶው ባለመብት, METROPOLITAN POLICE
ቀድሞ በናይጄሪያ ባለሥልጣን በነበረ ግለሰብ የተመዘበረውን 5.8 ሚሊዮን ዶላር [በወቅቱ የምንዛሬ ተመን ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ] የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለናይጄሪያ ተመላሽ አደረገ።
የናይጄሪያዋ ዴልታ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ጄምስ አይቦሪ እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 በዩኬ ውስጥ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተከሰው ነበር።
አቃቤ ሕግ እንደገለጸው ግለሰቡ ሲያስተዳድሯት ከነበረችው በነዳጅ ከበለጸገች ግዛቱ ከ165 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈዋል።
ግለሰቡ በመዘበሩት ገንዘብ የገዙት የግል ጀት በፍርድ ቤት እንዲወረሱ ከተወሰነባቸው ንብረቶች መካከል አንዱ ነው። 4.2 ሚሊዮን ዶላሩ ከአይቦሩ ባለቤት፣ እህትና ወኪል ተመላሽ የተደረገ ሲሆን እነሱም በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ይሁን እንጅ ሰውዬውን እናውቀዋለን የሚሉ ሰዎች የዘረፉት ገንዘብ "ይሄ ብቻ አይደለም" ብለዋል።
የናይጄሪያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቡበከር ማላሚ "የተመዘበረው ገንዘብ ተመላሽ መደረጉ "ናይጄሪያ ያላትን እውቅና እና መልካም ሥም የሚያሳይ" ነው ማለታቸውን ቃለ አቀባያቸው ተናግሯል።
ጄምስ ቦሪ 'በእንቁላሉ ጊዜ' ያልተቀጡ ሰው ነበሩ። ከአነስተኛ ገንዘብ ከማጨበርበር የጀመሩት ግለሰቡ፤ አሁን በከባድ የሀብት ምዝበራ ላይ ተገኝተዋል።
በዩኬ በአንድ መጋዘን በገንዘብ ተቀባይነት በሚሰሩበት ወቅት ገንዘብ ሲሰርቁ ተይዘው ነበር። ከዛም ወደ አገራቸው ተመልሰው ፖለቲከኛ ሆኑ።
ጄምስ በትንሹ የጀመሩት ስርቆት ለማስፋት ሥልጣኑ ተመቻቸው። እንደ አውሮፓውያኑ በ1991 የዴልታ አስተዳዳሪ ሲሆኑ በነዳጅ የበለጸገችውን ግዛት ካዝና ያራቁቱት ገቡ።
ታዲያ ይህን ገንዘብ ይዘው 'ስርቆትን በትንሹ ወደ ጀመሩባት' ብሪታኒያ አቀኑ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2005 በሌላ ሰው አማካኝነት የግል ጀት ለመግዛት ትዕዛዝ ሲሰጡ የዩኬ ፖሊስ ምርመራ ጀመረባቸው። ከተለያዩ የክስና የፍርድ ሂደቶች በኋላ የመዘበሩት ገንዘብ ወደ ናይጄሪያ እንዲመለስ ተደርጓል።












