የናይጄሪያዋ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሽቶዎች አጠቃቀም ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያዋ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሽቶዎች አጠቃቀም ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ሰጠች
በጸሎት ወቅት ሻማ እና ሽቶ በፈጠሩት እሳት አንድ ግለሰብ መሞቱን ተከትሎ ከናይጄሪያ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ማስጠንቀቂያ እንድትሰጥ ተገዳለች፡፡
ነጭ ልብስ በመልበስ በባዶ እግራቸው መንፈሳዊ አገልግሎት በመከታተል የሚታወቁ ምዕመናን ያሏት የሰለስቲያል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን በምዕራብ ናይጄሪያ ስሟ የገነነ ነው። በመላው ናይጄሪያ እና በአንዳንድ ሃገራትም ቤተ እምነቶች አላት፡፡
ካዮዴ ባድሩ ባለፈው ሰኞ ሌጎስ በሚገኘው ቤተክርስቲያን በግል በተዘጋጀ መንፈፈሳዊ ዝግጅት ላይ ሻማዎችን በማብራት ሲጸልዩ ነበር አደጋው የደረሰባቸው፡፡
የቤተክርስቲያኗ አባቶች ለባድሩ እየጸልዩ ነበር። ጸሎቱን የሚመሩት ቄስ ጠጋ ብለው ሽቶውን ሲነሰንሱበት አቅራቢያው ባለው ሻማ ምክንያት ሳይቀጣጠል አልቀረም ተብሎ ይታሰባል፡፡
አብዛኛዎቹ የእምነቱ ተከታዮች ተቀጣጣይ ከሆኑ እንደ ጥጥ እና ሐር ካሉ ጨርቆች የተሠሩ ነጭ ልብሶችን ይለብሳሉ። በዕለቱ ተመሳሳይ ነጭ ልብስ ለብሰው የነበሩት ባድሩን እሳቱ በፍጥነት ነበር ያቃጠላቸው፡፡
በደረሰው ቃጠሎ ህክምና ሲያገኙ ቆይተውም ሐሙስ ዕለት በሆስፒታል ህይወታቸው አልፏል፡፡
የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ቄስ ኢሞሌሚታን ኦጆ ከቢቢሲ ፒጂን ጋር በነበራቸው ቆይታ የጸሎቱን ፕሮግራሙን የመሩት አባት እና በቦታው የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡
ቤተክርስቲያኗ በጸሎት ፕሮግራሞች ወቅት ብርሃንን እና ጥሩ ሽታን ለማመላከት ሻማዎችን እና ሽቶዎችን ትጠቀማለች፡፡
ምዕመናን በአብዛኛው የራሳቸውን ሽቶ የሚጠቀሙ ቢሆንም አብያተ ክርስቲያኗ ለሽያጭ ያቀረበችውንም የሚጠቀሙ አሉ፡፡
ሽቶዎቹ ከመጠን በላይ የማይነሰነስ ሲሆን ምዕመናኑም ከውሃ ጋር እንዲቀልሏቸው ይመከራሉ፡፡ የባድሩ ሽቶ በዚህ ረገድ ስለመዘጋጀቱ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ቤተክርስቲያኗ ባሰራጨችው መግለጫ "ከበራ ሻማ ጋር ለመርጨት የተዘጋጁ መንፈሳዊ ሽቶዎች ውሃ ሊቀላቀልባቸው ይገባል" ብላለች፡፡
በመግለጫዋም "መንፈሳዊ ሽቶዎችን መርጨት ወይም ማፍሰስ የሰለስቲያል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓቶች አካል ያልሆነ ከውጭ የመጣ ባህል ነው" ስትል አክላለች፡፡
ቱጃሩ ባድሩ መኖሪያቸው ዱባይ ሲሆን ለምስጋና ስነ ስርዓት ነበር አባል ወደሆኑበት ቤተክርስትያን ያቀኑት፡፡
ሌላ ዘገባ ደግሞ ባለሃብቱ ወደ ናይጄሪያ ያቀኑት በእሳቸው ድጋፍ ትምህርታቸውን ከኪነጥበብ እና ቴክኖሎጂ አካዳሚ ያጠናቀቁ 40 ተማሪዎች የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው ሲል አስነብቧል፡፡
በቤኒን ፖርቶ-ኖቮ እአአ በ 1947 በሬቨረንድ ሳሙኤል ቢሌሆ ኦሾፋ የተቋቋመችው የሰለስቲያል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን በመላው ዓለም ቅርንጫፎች እንዳሏት ትናገራለች፡፡












