በትግራይ በመድፈር ወንጀል የተጠረጠሩ የመከላከያ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ

የጽዮን ማርያም ቤተ-ክርስቲያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በትናንትናው ዕለት በትግራይ ከተማ ስለተፈፀሙ ግድያዎች እና መደፈሮች በሰጠው መግለጫ በወንጀሉ የተሳተፉ የፌደራል እና መከላከያ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ ጾታን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም ወንጀል የመመርመር ስልጣን ያለው ክልሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተፈጸመውን ወንጀል እየመረመረ ያለው በክልሉ ፖሊስ አካላት መሆኑን ተናግረዋል።

ከክልሉ ፖሊስ በተገኘው መረጃ መሠረት የመድፈር ጥቃት ደርሶብናል ብለው ሪፖርት ያደረጉ ሴቶች ቁጥር 116 መሆኑን ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት መኖራቸውን አቶ ፍቃዱ ጸጋ ተናግረዋል።

አቶ ፍቃዱ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ድርጊቱን ፈጽመውታል የተባለው በግዳጅ ላይ እያሉ ስለሆነ ጉዳያቸው በጦር ፍርድ ቤት ይታያል ብለዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላትን በተመለከተ የክልሉ ፖሊስ ምርመራ አጠናቆ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወይም ደግሞ ለፍትሕ ቢሮ መዝገቡ ተላልፎ ተሰጥቷል ሲሉ አስረድተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ የፍትሕ ቢሮ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከሌሎች የፍትሕ አካላት ጋር በመተባበር የትኛውንም ወንጀል ፈጻሚ ሙያዊ ደረጃውን በጠበቀ መርምሮ ጥፋተኞችን ለሕግ ለማቅረብ ዝግጁነት አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት ወር ላይ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 የመደፈር ጥቃቶች ለጤና ተቋማት ሪፓርት መደረጋቸውን ገልጿል

ኮሚሽኑ በመቀለ ከሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ባገኘው መረጃ መሠረት፤ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በመቀለ ሆስፒታል 52፣ በአይደር ሆስፒታል 27፣ በአዲግራት ሆስፒታል 22፣ በውቅሮ ሆስፒታል 7 በአጠቃላይ 108 የመደፈር ጥቃቶች ለጤና ተቋማት ሪፖርት ተደርገዋል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በግጭት ወቅት የሚከሰት ወሲባዊ ጥቃት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ቡድን በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለው ወሲባዊ ጥቃት እንዲገታ በማሳሰብ መግለጫ ያወጣው በጥር ወር ላይ ነው።

የቡድኑ ልዩ ተወካይ ፕራምሊያ ፓተን ሁሉም አካላት ወሲባዊ ጥቃት እንዲገታ እንዲሁም ውጥረት እንዲረግብ የድርሻቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸው ይታወሳል

ልዩ ተወካይዋ "በመቀለ ከተማ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው የመደፈሩ ክስና በአጠቃላይ ከትግራይ ክልል የተሰሙት የወሲባዊ ጥቃት ክሶች እጅግ አሳስበውኛል" ብለዋል።

ጨምረውም "ሰዎች የገዛ ቤተሰባቸውን እንዲደፍሩ እየተገደዱና ይህን ካላደረጉ ጥቃት እንደሚደርስባቸው የሚጠቁሙ በጣም የሚረብሹ ሪፖርቶች ተሰምተዋል" ብለዋል።

ጥቅምት 24 2013 ዐዓ.ም በፌደራል መንግሥቱ እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሱ ወዲህ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መድረሳቸውን የተለያዩ አለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና ኢሰመኮ አስታውቋል።

ኢሰመኮ እና አምነስቲ ባወጧቸው መግለቻዎች ላይም በሕዳር ወር አጋማሽ ላይ በአክሱም በንፁኀን ዜጎች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ ይገኝበታል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባካሄደው ምርመራ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ አስታወቋል።

አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ ከ200 በላይ ሰዎች መግደላቸውን ገልጾ ነበር።

በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የኤርትራ ወታደሮች በኅዳር ወር በሁለት ቀናት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደላቸውን በተመለከተ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣውን ሪፖርት "ባልተሟላ መረጃና ውስን በሆነ የጥናት ዘዴ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው" ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ተችቷል።

ኤርትራ ወታደሮቿ አክሱም ውስጥ ፈጸሙት የተባለውን ግድያ በተመለከተ የወጣውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንደማትቀበለው ገልጻለች።

የፌደራል አቃቤ ሕግ በትናንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በሕዳር ወር 2013 ዐዓ.ም የተፈፀሙ ወንጀሎችን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።

በከተማዋ በተካሄደ ጦርነት የተተኮሰ መድፍ ዒላማውን ስቶ በመኖሪያ ቤት እና በዩኒቨርስቲው አካባቢ ወድቆ አምስት ሰዎች መሞታቸው በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

በተጨማሪም በከተማዋየተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም በነበረ አለመግባባት በፖሊስ አባላት በተተኮሰ ጥይት አንድ ሰው መገደሉን ሪፖርቱ ገልጿል።

መግለጫው አክሎም የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ከህዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሌላ ግዳጅ ከተማውን ለቆ እስከወጣበት እለት ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በአክሱም ከተማ መቆየቱን ያስረዳል።

ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ሰራዊቱ ለተጨማሪ ግዳጅ ከተማዋን ለቆ ሲወጣ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ የኤርትራ ሰራዊት በሁለት ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ተራራማ ቦታ ላይ መጥቶ መስፈሩንም ገልጿል።

አቃቤ ህግ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከተውጣጡ አባላት በተቋቋመ የምርመራ ቡድን አማካኝነት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች ተፈፅመዋል በሚሉ ለቀረቡለት ጥቆማዎች ምላሽ ለመስጠት በአካባቢው ተገኝቶ የወንጀል ፈፃሚዎቹን ማንነት ለመለየት የሚያስችል ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኤርትራ ሰራዊት በአካባቢው ከሰፈረ በኋላ የህወሃት ኃይሎች የኤርትራ ሰራዊት ለመዋጋት ሳይሆን እጅ ለመስጠት ይፈልጋል በማለት ከአዴት የመጡ የህወሃት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላትና በከተማዋ ውስጥ ካሉ 1500 የሚጠጉ የተኩስ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ጋር በመሆን ወደ አክሱም እንደገቡ መግለጫው አስፍሯል።

መግለጫው አክሎም በበረሃ የነበሩት የቀድሞ የአክሱም ከንቲባ በአክሱም ከተማ ከህዳር 01-09 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ህወሃት የአንድ ቀን የመሳሪያ ተኩስ ስልጠና ለሰጣቸው 1 ሺህ 500 ወጣቶች መሳሪያ እንዲከፋፈል ትዕዛዝ ደብዳቤ በመፃፍ አስተላልፈዋል ብሏል።

እነዚህ መሳሪያዎች "ከሰሜን እዝ ላይ የተሰረቁትን" ጨምሮ በአምስት ቦታዎች ላይ የተከማቹ የጦር መሳሪያዎች ናቸው ይላል የአቃቤ ህግ መግለጫ። እነዚህ አካካላት ተባብረው ከጥዋቲ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 8 ሰዓት ውጊያ ላይ ነበሩ የሚለው መግለጫው የመከላከያ ሰራዊቱ አጋዥ ኃይል በቦታው ሲደርስ ወደ ከተማዋ ሸሽተው መግባታቸውንም በምርመራ ማረጋገጡን አስፍሯል።

አቃቤ ህግ እንደሚለው የምርመራ ቡድኑ የጦር መሳሪያ ከደረሳቸው እና ካልደረሳቸው ወጣቶች እንዲሁም ከልዩ ኃይል አባላት የምስክርነት ቃል ነው ይህንን ማረጋገጥ የቻልኩት ብሏል።

የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት ቡድኑ የ95 ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን ጠቅሶ የ93 ሰዎች ህይወት ማለፉንም አስፍሯል። የሟቾቹን ማንነት በተመለከተ መግለጫው እንዳሰፈረው "ማቾቹምወታደራዊ የደንብ ልብስ ባይለብሱም በአብዛኛው በጦርነቱ የተሳተፉ ሰዎች ስለመሆናቸውም በምርመራው የተረጋገጠ ጉዳይ ነው" በማለት አትቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ መጋቢት ላይ ባወጣው መግለጫ በአክሱም ከተማ በኤርትራ ወታደሮች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል በማለት ገልጿል።

ኮሚሽኑ በአክሱም ከተማ ውስጥ ስለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ያካሄደው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው የተፈጸሙት ድርጊቶች "ተራ ወንጀሎች ሳይሆኑ የዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና መርሆዎችን የሚጥሱ ናቸው" በማለት በአጠቃላይ በክልሉ ውስጥ የተሟላ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

በዚህም በኤርትራ ሠራዊት በአክሱም ከተማ ውስጥ የፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት "ምናልባት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ስለሚችል" ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

በከተማዋ በግጭቱ ተሳታፊ ያልነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን አመልክቶ በወታደራዊ ኢላማነት አስፈላጊነታቸው ሊገመገሙ የማይችሉ የሰላማዊ ሰዎች ንብረቶች፣ በሐይማኖት ተቋማትና በሆስፒታሎች ላይ ጭምር ሆን ተብሎ ዝርፊያና ጉዳት መድረሱን መግለፁ የሚታወስ ነው።