ኮሮናቫይረስ፡በደርዘን የሚቆጠሩ አስከሬኖች በህንድ ወንዝ ዳርቻ ላይ ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሰሜናዊ ህንድ በጋንጀስ ወንዝ ዳርቻ ቢያንስ የ 40 ሰዎች አስከሬን በውሃ ተገፍቶ መገኘቱን ባለስልጣናት ገለጹ፡፡
አስከሬኖቹ በቢሃር እና በኡታር ፕራዴሽ ግዛቶች ድንበር አቅራቢያ መገኘታቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል፡፡
አስከሬኖቹ እንዴት እንደመጡ ግልፅ ባይሆንም የአከባቢው የመገናኛ ብዙሃን የኮቪድ-19 ሰለባዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል፡፡
አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ እስከ 100 የሚደርሱ አስከሬኖች መገኘታቸውን ጠቅሰው አስከሬኖቹ በወንዙ ውስጥ ለብዙ ቀናት እንደቆዩ ምልክቶች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
የአከባቢው ባለሥልጣን አሾክ ኩማር የአከባቢውን ነዋሪዎችን ከጠየቁ በኋላ ለቢቢሲ እንደገለጹት "አስከሬኖቹ ከኡታር ፕራዴሽ የመምጣት ዕድል አላቸው" ብለዋል፡፡
አስከሬኖቹ እንደሚቀበሩ ወይም እንደሚቃጠሉ ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣናት አስከሬኖቹ ያበጡ እና በከፊል የተቃጠሉ እንደሆኑና ምናልባትም የኮሮናቫይረስ ተጎጂዎችን የማቃጠል ተግባር አካል ሆነው ወደ ወንዙ የደረሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ መግለጻቸውን የህንዱ የኤንዲቲቪ የዜና አውታር ዘግቧል፡፡
አንዳንድ የአከባቢው ነዋሪዎች እና ጋዜጠኞች ለቢቢሲ ሂንዲ እንደተናገሩት ለእሳት ማቃጠያ የሚሆን የእንጨት እጥረት እና ከቀብር ሥነ ሥርዓቶች ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣው ወጪ አንዳንድ ቤተሰቦች በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ዘመዶቻቸውን ወደ ወንዝ እንዲጥሉ እያደረገ ነው፡፡
የአከባቢው ነዋሪ የሆኑት ቻንድራ ሞሃን "የግል ሆስፒታሎች ሰዎችን እየዘረፉ ነው። ብዙ ሰዎች ለካህናት እና በወንዙ ዳርቻ ላይ ለማቃጠል የሚጠየቀውን ገንዘብ አይኖራቸውም። አስከሬኑን በአምቡላንስ ለመውሰድ ብቻ 27 ዶላር ስለሚጠየቅ የመጨረሻው አማራጫቸው አስከሬኑን በወንዙ ውስጥ መጣል ነው" ብለዋል፡፡
ኡታር ፕራዴሽ በሕንድ ውስጥ በጣም ብዙ የህዝብ ቁጥር ያለው ክልል ነው ፡፡
ሁለተኛው የኮቪድ ማዕበል ሕንድን እያመሳት ሲሆን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቫይረሱ ህይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ የሬሳ ማቃጠያ ስፍራዎች ሞልተዋል፡፡
አገሪቱ አሁን የዓለም ዋነኛ ወረርሽኝ ማዕከል ሆናለች፡፡
ሕንድ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከ 22.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ ሲያዙ 246,116 የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ አመልክቷል፡፡
ባለሙያዎቹ ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አላቸው












