ሲቲ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የሊግ ዋንጫን በማንሳት ታሪክ ሠራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማንቸስተር ሲቲ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የሊግ ዋንጫን በማንሳት ታሪክ ሲሰራ ቶተንሃም አሁንም ዋንጫ አልባው ቡድን ሆኗል።
ሁለቱ ቡድኖች በግዙፉ ዌምብሊ ስታድየም ተገናኝተው ሲቲ በአያሜሪክ ላፖርት ጎል አንድ ለባዶ በመርታት ዋንጫ አንስቷል።
ላፖርት ጨዋታው ሊገባደድ 8 ደቂቃ ሲቀረው ከኬቪን ደ ብራይን የተሻማለትን ኳስ በጭንቅላቱ ከመረብ በማዋሃድ የቶተንሃምን የዋንጫ ተስፋ አጨልሟል።
ባለፈው ሳምንት ሰኞ ጆዜ ሞውሪንሆን ያባረሩት ቶተንሃሞች በጨዋታው ተበልጠው ታይተዋል።
ጨዋታው ሁለት ሺህ ከእያንዳንዱ ቡድን እንዲሁም አራት ሺህ ተጨማሪ ተመልካቾች በአጠቃላይ 8 ሺህ ደጋፊዎች በተገኙበት ነበር የተካሄደው።
ሲቲ ይህን ዋንጫ አራት ጊዜ በተከታታይ በማሸነፍ የሊቨርፑልን የ1980ዎቹን ክብረ ወሰን ተጋርቷል።
አልፎም ዋንጫውን በአጠቃላይ 8 ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ከሊቨርፑል ጋር እኩል ታሪክ መሥራት ችሏል።
"ተጨዋቾቼ እያደረጉ ያሉት ይህን ነው። ለመጪው ዘመን የሲቲ ተጫዋቾች ታሪክ እየሠሩ ነው የሚሄዱት" ሲሉ የሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ አስተያየት ሰጥተዋል።
"ወደ ፍፃሜው ለመድረስ ማንቸስተር ዩናይትድንና አርሰናል ረትተን ነው የመጣነው። ስለዚህ ዋንጫውን ማንሳት ይገባናል ማለት እንችላለን።"
ጉዋርዲዮላ ዋንጫውን ሲያነሱ ፊታቸው በደስታና በሻምፓኝ ረስርሶ ታይቷል።
ሲቲ ዘንድሮ አራት ዋንጫ ለመብላት የነበራቸው ተስፋ ባለፈው ሳምንት ከቼልሲ ጋር የኤፍ ዋንጫ ፍልሚያን በመሸነፋቸው ከሽፏል።
ነገር ግን ቶተንሃም የካራባዎ ዋንጫን ከመብላት የሚያግዳቸው ቡድን ሆኖ አልተገኘም።
ፔፕ ጉዋርዲዮላ ይህ በአሠልጣኝነት ዘመናቸው 30ኛ ዋንጫቸው ነው። የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ አንደኛውን እጀታ የጨበጡ ይመስላል። ቻምፒዮንስ ሊግ ለመብላትም የማይወጡት ተራራ ያለ አይመስልም።
ነገሮች እየተሳኩለት የማይመስለው ቶተንሃም በሦስት ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ፍፃሜ ደርሶ ዋንጫው ለተቀናቃኝ ቡድን አስረክቦ ተመልሷል።
የዋንጫ ጨዋታ እያላቸው ፖርቹጋላዊውን አሠልጣኝ ሆዜ ሞውሪንሆን ያባረሩት የቶተንሃሙ ሊቀ-መንበር ዳንኤል ሌቪ ቡድናቸው የፈረሰው ሱፐር ሊግን መቀላቀሉ አስተችቷቸው ነበር።
ሌቪ፤ ቡድናቸው ለዋንጫ ደርሶ ልምድ ያላቸውን አሠልጣኝ አባረው ወጣት መተካታቸው ከደጋፊዎች ተቃውሞ እንዲደርሳቸው ምክንያት ሆኗል።
ከቶተንሃም ጋር ዋንጫ አንስቶ የማያውቀው የእንግሊዙ አምበል ሃሪ ኬን ከጉዳት ተመልሶ በፍፃሜው ቢጫወትም ጫና መፍጠር አልቻለም።
ደቡብ ኮሪያው ሄውንግ-ሚን ሰን ከፍፃሜው በኋላ ሲያነባ ታይቷል።
ቶተንሃም አምስት ጊዜ ለፍፃሜ ደርሰው ሳያሸንፉ ቀርተዋል። ባለፉት አራት የፍፃሜ ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር እንኳን አልቻሉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images















