ስድስቱ 'ኃያላን' የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከአዋዛጋቢው ሱፐር ሊግ እራሳቸውን አገለሉ

የቼልሲ ደጋፊ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ መቋቋምን ተቃውመዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስድስቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ሃሳባቸውን በመቀየር እርሳቸውን አዲስ ከሚመሰረተው የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ማግለላቸውን አስታወቁ።

በአዲስ መልክ ሊዘጋጅ በታሰበው የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ መስራች አባል የነበሩት አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል፣ ማንችስተር ዩናይት፣ ማንችስተር ሲቲ እና ቶተነሃም በውድድሩ እንደማይሳተፉ ይፋ አድርገዋል።

ማንቸስተር ሲቲ ከአውሮፓ ሱተር ሊግ እራሱን ያገለለ የመጀመሪያው የእንግሊዝ ክለብ ሲሆን ቼልሲ ቀደም ብሎ ለመልቀቅ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ ነበር ተብሏል።

ቀሪዎቹ አራት ክለቦችም በውድድሩ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።

12 የአውሮፓ ክለቦች በመስራችነት የአውሮፓ ሱፐር ሊግን እንጀምራለን የማለታቸው ዜና የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር።

የአርሰናል ቦርድ በሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ማቀዴን አቁሜያለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ላይ፤ በሊጉ ለመሳተፍ መወሰኑ በደጋፊዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አለመገመቱን እና ሱፐር ሊጉን ለመቀላቀል የወሰነውም ክለቡ ብቻውን ላለመቅረትና የክለቡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ አንደሆነ ገልጿል።

"ዓላማችን ሁሌም ለዚህ ታላቅ የእግር ኳስ ክለብ ትክክለኛውንና ጠቃሚ ውሳኔ ማስተላላፍ ነው። አሁን ላይ ትክክለኛውን ውሳኔ አላስተላለፍንም፤ ኃላፊነቱንም እንወስዳለን" ብሏል ቦርዱ።

ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ እግር ኳስ እያጋጠሙት ያሉትን ጋሬጣዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመፍታትና መፍትሄዎችን ለማበጀት ከሁሉም የእግር ኳስ ማህበረሰብ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል።

ሌላኛ ክለብ ሊቨርፑል የአውሮፓ ሱፐር ሊግን ለመቀላለቀል መወሰኑን ተከትሎ ከክለቡ ውስጥም ሆነ ውጪ የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ሃሳባቸውን ሲያጋሩ እንደነበርና በመጨረሻም ይህ አዲሱን ሊግ ላለመቀላለቅ መወሰኑን ገልጾ ሁሉንም አካላት ለአበርክቷቸው አመስግኗል።

የቶተንሀም ሊቀመንበር ዳንኤል ሌቪ በበኩሉ የክለቡን የገቢ ምንጭ ለመጨመርና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ በአዲስ መልክ የተዘጋጀው ውድድር ላይ ለመሳተፍ እንደተወሰነ ገልጿል።

"ውሳኔያችንን ተከትሎ የሚመለከታቸው በሙሉ ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው ገልጸውልናል። ልናመሰግናቸው እንወዳለን" ብሏል።

ቼልሲ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩን ለማጤን ጊዜ እንወሰደና ለእግር ኳሱና ለደጋፊዎች ጥቅም ሲል ላለመሳተፍ መወሰኑን አስታውቋል።

የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጫፍ የደረሱት ማንችስተር ሲቲዎች የአውሮፓ ሱፐር ሊግን ለመመሠረት የተጀመረውን ሂደት ለመልቀቅ በይፋ ሰነድ ማዘጋጀት እንደጀመሩ ገልጸዋል።

12ቱ ክለቦች የራሳችን የሆነ ሊግ እንጀምራለን ማለታቸው ደግሞ በመላው ዓለም በተለይ አውሮፓውያንን በጣም ያስገረመና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ነበር። የቀድሞ ተጫዋቾች፣ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች እና መሪዎችም ጭምር ውሳኔውን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንደሚሳተፉ ያስታወቁ ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ በርካታ ተጫዋቾች በበኩላቸው በውሳኔው ደስተኞች እንዳልሆኑ ሲገልጹ ነበር።

የሊቨርፑሉ አምበል ጆርዳን ሄንደርሰን በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፈው መልዕክት ሁሉም የክለቡ ተጫዋቾች በአውሮፓ ሱፐር ሊግ መሳተፍ እንደማይፈልጉ ገልጿል።

አሰልጣኙ የርገን ክሎፕም ቢሆኑ በዚህ ሀሳብ ደስተኛ እንዳልሆኑ እና ለእግር ኳስ እድገት እንደማይጠቅም ገልጸው ነበር።

የቼልሲ ሰጋፊዎች በስታንፎርድ ብሪጅ ስታዲየም አቅራቢያ በመገኘት ክለባቸው በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ መወሰኑን ተቃውመዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የቼልሲ ሰጋፊዎች በስታንፎርድ ብሪጅ ስታዲየም አቅራቢያ በመገኘት ክለባቸው በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ መወሰኑን ተቃውመዋል።

በአዲሱ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እቅድ መሰረት መስራቾቹ ክለቦች ማለትም አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ቶተንሀም ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ ሪያል ማድሪድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድና ባርሴሎና ከስፔን እንዲሁም ጁቬንቱስ፣ ኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን ከጣልያን በውድድሩ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ነበር።

አዲሱ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ከቴሌቪዥን ሽያጭ ብቻ በዓመት እስከ 4.8 ቢሊየን ዶላር ድረስ ሊያስገኝ እንደሚችል ተገምቶ የነበረ ሲሆን ይህም አሁን ላይ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከሚገኘው ከእጥፍ በላይ ነው።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሴፍሪን የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች እንደማይሳተፉ መግለጻችውን በደስታ ተቀብለውታል።

"አሁን ወደቀደመው የእግር ኳስ አካሄድ እንመለሳለን። እነዚህ ክለቦች ለምናዘጋጃቸው ውድድሮች ብቻ ለመላው የአውሮፓ እግር ኳስ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖራቸው አውቃለሁ" ብለዋል።

"በዚህ ሰአት ወሳኙ ነገር ወደፊት መጓዝ ነው። አደጋ አጋጥሞት የነበረውን አንድነታችንን መመለስና እግር ኳስን ማጣጣም መጀመር አለብን" ሲሉም ጨምረዋል።

በእቅዱ መሠረት የአውሮፓ ሱፐር ሊግ በየዓመቱ ነሀሴ ወር ላይ የሚካሄድ ሲሆን ጨዋታዎቹም የሳምንቱ አጋማሽ ላይ ይደረጋሉ። ተሳታፊዎቹ 20 ቡድኖችም በሁለት ምድቦች ተከፍለው በደርሶ መልስ ጨዋታ ይፋለማሉ የሚል እቅድ ተይዞ ነበር።

ስድስቱ የእንግሊዝ ክለቦች ከዚህ ሊግ እራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ የሊጉ እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ግልጽ አይደለም።