ልዕልት ላቲፋ፡ የተባበሩት መንግሥታት ልዕልቷ በሕይወት ስለመኖሯ ማረጋገጫ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, ልዕልት ላቲፋ
የዱባይ ገዢ ልጅ ልዕልት ላቲፋ አል ማክቱም በሕይወት መኖሯን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ የተባበሩት መንግሥታት ጠየቀ።
ተመድ ማስረጃውን እንዲያቀርብ የጠየቀው የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መንግሥትን ነው።
የተመድ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ማክሰኞ በጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ልዕልት ላቲፋ፤ "በአስቸኳይ" መለቀቅ አለባትም ብለዋል።
ልዕልት ላቲፋ በጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ከዱባይ ለመሸሽ ሞክራ ነበር። ቢቢሲ ፓኖራማ ይፋ ባደረገው ቪዲዮ መሠረት ኮማንዶዎች አደንዝዘው ወደ እስር ቤት እንደወሰዱዋት ልዕልቷ ተናግራለች።
ከዚህ ቀደም የዱባይ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ልዕልት ላቲፋ ደኅንነቷ በተጠበቀ ሁኔታ "ቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላት ነው" ብለው ነበር።
የተመድ ባለሙያዎች ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት ልዕልት ላቲፋ ዕጣ ፈንታ ላይ "ሳይዘገይ ትርጉም ያለው መረጃ እንዲሰጥ" ጥሪ አቅርበዋል።
"የታሰረችበትን ሁኔታ ገለልተኛ ቡድን እንዲያጣራ እና በፍጥነት ከእስር እንድትለቀቅም" ጠይቀዋል።
"በኤሚሬትስ ባለሥልጣናት የተሰጠው መግለጫ 'በቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላት' መሆኑን የሚያመለክት መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም" ብሏል መግለጫው።
መግለጫው አክሎም "በየካቲት ወር ላቲፋ ከፍላጎቷ ውጭ ነፃነቷን እንደተነፈገች የሚገልጸውን ቪዲዮ ተከትሎ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጠን ቢጠየቅም ባለሥልጣናቱ ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃ አልተሰጡም" ብሏል።
በቢቢሲ ፓኖራማ የካቲት ወር ባገኘው ቪዲዮ መሠረት ልዕልት ላቲፋ የህክምና እርዳታ በማታገኝበት እና "ወደ እስር ቤት በተለወጠ ቪላ" ውስጥ ታግታ እንደምትገኝ ተናግራለች።
የላቲፋ አባት ሼህ መሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም የዱባይ ገዥ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ በዓለም ላይ እጅግ ሀብታም የአገር መሪዎች አንዱ ናቸው።
ስለ ልዕልት ላቲፋ ምን እናውቃለን?
ልዕልት ላቲፋ የካቲት 2018 አዲስ ሕይወት ለመጀመር በጓደኞቿ እርዳታ ከዱባይ ለማምለጥ እንደሞከርች ትናገራለች።
ከማምለጧ በፊት ጥቂት ቀደም ብሎ በተቀረፀ ቪዲዮ "መኪና መንዳት አልተፈቀደልኝም፣ ዱባይ ውስጥም መጓዝ ሆነ መውጣት በጭራሽ አልተፈቀደልኝም" ብላለች።
ከቀናት በኋላ ግን ልዕልቷ ከተባበሩት ኤሜሬትስ ለማምለጥ ስትሞክር ሕንድ ውቅያኖስ ላይ በጀልባ ስትጓዝ በኮማንዶዎች ተያዝኩ ትላለች። ወዲያውም ዱባይ እንድትመለስ ተደርጓል።
አባቷ ለእሷ የሚጠቅም እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፈው ወር ከዱባይ ንጉሣዊ ቤተሰብ በተሰጠ መግለጫ በቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላት መሆኑን በድጋሚ ተገልጿል።
"ላቲፋ መሻሻሏን የቀጠለች ሲሆን በተገቢው ጊዜ ወደ መደበኛ ህይወት እንደምትመለስ ተስፋ አለን" ብለዋል።
ከተያዘች ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በድብቅ እንደተሰጣት የተናገረችውን ስልክ በመጠቀም ልዕልት ላቲፋ ለበርካታ ወራት ብዙ ቪዲዮዎችን ቀረጻለች።
ልዕልቷ ብቸኛ ልትዘጋ የምትችለው በር የመታጠቢያ ቤቱን በመሆኑ ቪዲዮዎቹን እዛ ቀርጻቸዋለች። በመልእክቶቿም የሚከተለውን በዝርዝር ገልጻለች
- ልታመልጥ ስትሞክር ከጀልባዋ ላይ ሲያወርዷት ወታደሮቹን በመቃወም "ረግጣ እና ታግላ" አንድ የኤሚሬትስ ኮማንዶን ክንድ እስኪጮህ ድረስ ነክሳለች።
- ከተረጋጋች በኋላ ወደ በግል ጄት እየተጓዘች እያለ ራሷን የሳተች ሲሆን ዱባይ እስክትደርስም አልነቃችም ነበር
- በፖሊስ ጥበቃ በሚደረግበት፤ መስኮቶቹና በሮቹ በተዘጉ ቪላ ውስጥ ያለህክምና እና የህግ ድጋፍ ብቻዋን ታስራለች።















