የዱባይ ንጉሣዊ ቤተሰብ ልዕልት ላቲፋ "በቤት ውስጥ እንክብካቤ እያገኘች ነው" አለ

ልዕልት ላቲፋ

የዱባይ ንጉሣዊ ቤተሰብ ልዕልት ላቲፋ "በቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላት ነው" ሲል አስታወቀ።

ቢቢሲ ልዕልቲቷ "በአባቴ ታግቻለሁና አድኑኝ" ስትል የተማፀነችበትን ተንቀሳቃሽ ምሰል ካገኘ በኋላ የዱባዩ መሪ ልጅ ልዕልት ላቲፋ በሕይወት መኖሯን ለማረጋገጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስረጃ ጠይቆ ነበር።

የንጉሣዊ ቤተሰቡ በመግለጫቸው ላይ "ጤንነቷ እየተሻሻለ ነው እናም ጊዜው ሲደርስ ወደ ቀደመው ሕይወቷ ትመለሳለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

ነገር ግን ከቤተሰቧ ላቲፋ በሕይወት መኖሯን የሚያሳይ ፎቶም ሆነ ተንቀሳቃሽ ምስል ወይንም ደግሞ ስላለችበት ሁኔታ የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ አልቀረበም።

የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለቢቢሲ ጉዳዩን እንደሚመለከቱት የገለፁ ሲሆን፣ "የሰብዓዊ መብትን በአንክሮ ነው የምንከታተለው። ሁኔታውን በቅርበት፣ ከሌሎች አጋሮቻችን ጋር በመሆን እንከታተለዋለን" ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውመን ራይትስ ዎች ኃላፊ ኬኔት ሮት በበኩላቸው ንጉሣዊ ቤተሰብ ያወጣውን መግለጫ "ለመሸፋፈን የቀረበ" በሚል ያጣጣሉት ሲሆን፣ ላቲፋ ራሷ እስካልተናገረች ድረስ የዱባይ ንጉሣዊ ቤተሰብን ማንም አያምንም ብለዋል።

ላቲፋ ነጻ እንድትወጣ ዘመቻዎችን እያደረገ የሚገኘው ቡድን በበኩሉ በንጉሣዊ ቤተሰቡ መግለጫ ላይ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጋር ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቋል።

ንጉሣዊ ቤተሰቡም ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ በመነሳት እምነት የሚጣልበት አለመሆኑንም አክሎ ገልጿል።

በመግለጫቸውም ላይ የዱባይ ባለስልጣናት ለስቃይ ልትጋለጥና ማደንዘዣ ሊሰጣት ይችላል ሲሉ ፍርሃታቸውን ገልፀዋል።

የ'ፍሪ ላቲፋ' ዘመቻ አስተባባሪዎች "አሁን ገለልተኛ የሆነ የተባበሩት መንግሥታት አካል ወደ ዱባይ ተንቀሳቅሶ የመጎብኛው ወሳኝ ጊዜ ነው። እንዲሁም ላቲፋ ወደምትመርጠውና ደህንነት ወደሚሰማት አገር ሊያመጧት ይገባል" ብለዋል።

የንሣዊው ቤተሰብ ምላሽ የተሰማው በለንደን ከሚገኘው የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ኤምባሲ በኩል ነው።

"ሼይካ ላቲፋን በተመለከተ ምንም እንኳ የቀረቡት ዘገባዎች በሙሉ ያለችበትን ሁኔታ በትክክል የሚያሳዩ ባይሆኑም፣ ስለደህንነቷ ሁሉ የተጨነቁትን ማመስገን እንፈልጋለን" ይላል መግለጫው።

አክሎም "ቤተሰቦቿ ልዕልት ላቲፋ በሀኪሞችና በቤተሰቦቿ በቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላት እንደሆነ አረጋግጠዋል" ይላል።

የልዕልት ላቲፋ አባት ሼክ ሞሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቶም፣ የዱባይ ገዢ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፣ በዓለማችን ላይ ከናጠጡ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ልዕልት ላቲፋ እኤአ በ2018 የካቲት ወር ከዱባይ ለመውጣት እና አዲስ ሕይወት ለመጀመር በጓደኛዋ ርዳታ ሞክራ ነበር።

ከማምለጧ በፊት በለቀቀችው ተንቀሳቃሽ ምስል "መኪና መንዳት አይፈቀድልኝም። ዱባይን ለቅቄ እንድሄድ አይፈቀድም" ብላ ነበር።

ነገር ግን ከቀናት በኋላ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በኮማንዶዎች በቁጥጥር ስር ልትውል ችላለች። ከዚያም ወደ ዱባይ እንድትመለስ የተደረገ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

በወቅቱ አባቷ ለደህንነቷ ምቹ በሆነ ሁኔታ ነች ብለው ነበር።

ከዚህ ቀደም ዱባይም እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ልዕልት ላቲፋ ከቤተሰቧ ጋር ደህንቷ ተጠብቆ ትገኛለች ብለው ነበር።

2px presentational grey line

በቅርቡ የወጣው ቪዲዮ የተቀረፀው ተይዛ ወደ ዱባይ እንድትመለስ ከተደረገች ከአመት በኋላ በነበሩት ወራት ውስጥ ነው።

ቪዲዮውንም በመታጠቢያ ቤት ሲሆን የቀረፀችው ይህም ከውስጥ መቆለፍ የምትችለው ክፍል እሱ ብቻ ስለሆነ ነው ተብሏል።

ታግታና በእስር ላይ እንዳለች በገለፀችበት ቪዲዮ የዘረዘረቻቸው ጉዳዮች፦

  • ከጀልባ ሊያስወርዷት የሞከሩትን ወታደሮች በመፈራገጥና በመማታት ልታመልጥ እንደሞከረችና አንደኛውን የኤምሬትስ ኮማንደር እስኪጮህ ድረስ ነክሳዋለች።
  • ማደንዘዣ ከወጓት በኋላ ራሷን ሙሉ በሙሉ የሳተች ሲሆን በግል አውሮፕላን ውስጥ አሳፍረው ወደ ዱባይ ወስደዋታል። ዱባይ እስክትደርስ አልነቃችም ነበር።
  • በአንድ ቪላ ውስጥ ያለ ምንም የህክምናም ሆነ ሕጋዊ እርዳታ ተቆልፎባት እንደሚገኝና በፖሊስ እንደምትጠበቅም ይፋ አድርጋለች።

የላቲፋን መያዝና እስር አስመልክቶ ያጋለጡት ቅርብ ጓደኛዋ ቲና ጁሃይነን፣ የአጎቷ ልጅ ማርከስ ኢሳብሪና ተሟጋቹ ዴቪድ ሃይ ሲሆኑ ሁሉም ላቲፋ ነፃ እንድትወጣ ዘመቻን እያካሄዱ ይገኛሉ።

የላቲፋ ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ ስላሰጋቸው ቪዲዮውን አሁን ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።