የዱባዩ መሪ ልጅ "በአባቴ ታግቻለሁ" አለች

የፎቶው ባለመብት, Princess Latifa
የዱባዩ መሪ ልጅ አባቷ እንዳገቷትና ለህይወቷ በከፍተኛ ሁኔታም እንደምትሰጋ በቅርቡ በወጣ ሚስጥራዊ ቪዲዮ ላይ ገልፃለች።
በአሁኑ ወቅት በአንድ ቪላ ውስጥ ተዘግቶባት እንምትገኝና ነፃ አውጡኝ ስትል ተማፅናለች።
ልዕልት ላቲፋ አል ማክቱም ከሶስት አመታት በፊት ከአገር ሸሽታ ልትወጣ ሞክራም ነበር።
በውቅቱም በጀልባ ተሳፍራ ልታመልጥ የነበረ ሲሆን የጦር ኮማንዶዎች አፍነው እንደወሰዷትና በእስር ላይ እንደምትገኝ ልዕልት ላቲፋ አል ማክቱም ተናግራለች።
አጠር ያለ ሚስጥራዊ የቪዲዮ መልዕክቷን ተከትሎ ጓደኞቿ የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ እንዲገባ እየጠየቁ ነው።
የዱባይም ሆነ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም በቤተሰቦቿ እንክብካቤ ውስጥ እንደሆነችና ደህንነቷም የተጠበቀ ነው የሚል መግለጫ ሰጥተው ነበር።
የቀድሞ የተባባሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ልዩ መልዕክተኛ ሜሪ ሮቢንሰን ከሶስት አመት በፊት ልዕልቲቷን ባገኟት ወቅት "የተረበሸች ወጣት" በሚል የገለጿት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን በልዕልቲቱ ቤተሰብ በአሳዛኝ ሁኔታ እንደተሸወዱ ተናግረዋል።
የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነርና የአየርላንድ ፕሬዚዳንት ልዕልት ላቲፋ ያለችበት ሁኔታና ቦታ እንዲገለፅ አለማቀፋዊ ጫና እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
"የላቲፋህ ሁኔታ በጣም አስጨናቂ ነው። ሁሉ ነገር ተዳፍኖ ነው ያለው። ምርመራ ሊከፈት ይገባል" ብለዋል።
የላቲፋህ አባት ሼክ መሃመድ ቢን ራሺል አል ማክቱም በአለማችን ካሉ መሪዎች አንደኛ ሃብታም ሲሆኑ ፤ የዱባይ መሪ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው።
በቅርቡ የወጣው ቪዲዮ የተቀረፀው ተይዛ ወደ ዱባይ እንድትመለስ ከተደረገች ከአመት በኋላ በነበሩት ወራት ውስጥ ነው። ቪዲዮውንም በመታጠቢያ ቤት ሲሆን የቀረፀችው ይህም ከውስጥ መቆለፍ የምትችለው ክፍል እሱ ብቻ ስለሆነ ነው ተብሏል።
ታግታና በእስር ላይ እንዳለች በገለፀችበት ቪዲዮ የዘረዘረቻቸው ጉዳዮች፦
- ከጀልባ ሊያስወርዷት የሞከሩትን ወታደሮች በመፈራገጥና በመማታት ልታመልጥ እንደሞከረችና አንደኛውን የኤምሬትስ ኮማንደር እስኪጮህ ድረስ ነክሳዋለች።
- ማደንዘዣ ከወጓት በኋላ ራሷን ሙሉ በሙሉ የሳተች ሲሆን በግል አውሮፕላን ውስጥ አሳፍረው ወደ ዱባይ ወስደዋል። ዱባይ እስክትደርስ አልነቃችም ነበር።
- በአንድ ቪላ ውስጥ ያለ ምንም የህክምናም ሆነ ህጋዊ እርዳታ ተቆልፎባት እንደሚገኝና በፖሊስ እንደምትጠበቅም ይፋ አድርጋለች።
የላቲፋን መያዝና እስር አስመልክቶ ያጋለጡት ቅርብ ጓደኛዋ ቲና ጁሃይነን፣ የአጎቷ ልጅ ማርከስ ኢሳብሪና ተሟጋቹ ዴቪድ ሃይ ሲሆኑ ሁሉም ላቲፋ ነፃ እንድትወጣ ዘመቻን እያካሄዱ ይገኛሉ።
የላቲፋ ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ ስላሰጋቸው ቪዲዮውን አሁን ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ላቲፋ በዱባይ መስኮትና በሩ በተዘጋበት ቤት እንዲሁም ፖሊሶች በሚጠብቁት ቪላ ውስጥ እያለች ማግኘት ችለው እንደነበር ተገልጿል።
ቢቢሲም ቢሆን ልዕልቲቷ የታገተችበትን ቦታ በገለልተኛ አካል ማጣራት ችሏል።
ሼክ መሃመድ ዱባይን እንድትበለፅግ ማድረጋቸው ቢያስወድሳቸውም አስተዳደራቸው ተቃዋሚዎችን ዝም በማሰኘት እንዲሁም የፍትህ ስርአቱ ሴቶችን በማግለል ይተቻሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በልጃቸው ልዕልት ላቲፋና በባለቤታቸው ፕሪንሰስ ሃያ ቢንት አሊ ሁሴን አያያዝ ከፍተኛ ትችት ይቀርብባቸዋል። ባለቤታቸው ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ከሁለት አመት በፊት ወደ ለንደን አቅንተዋል።
የ35 አመቷ ልዕልት ላቲፋ መጀመሪያ ልታመልጥ የሞከረችው በ16 አመቷ ሲሆን በወቅቱም ሄርቬ ጃውበርት ከተባለ ፈረንሳያዊ ነጋዴ ጋር እቅድም ታቅዶ ነበር። በወቅቱም ስፖርት ታሰለጥናት የነበረችው አስተማሪም አማካኝነት ነበር የማምለጥ እቅዱ የተወጠነው።
ከሰባት አመታት በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 2018 ልዕልት ላቲፋና አስተማሪዋ በጀልባ አለም አቀፍ ውሃዎች የደረሱ ሲሆን፤ የአሜሪካ ሰንደቅ አላማ ያለበት መርከብም እየጠበቁ ነበር።
ከስምንት ቀናት በኋላ ወደ ህንድ አካባቢ ሲደርሱ የጦር ኮማንዶዎች ጀልባዋን በቁጥጥር ስር አውለዋታል። የስፖርት መምህሯ እንደምትለው አስለቃሽ ጋዝ በማፈንዳት ላቲፋ ከተደበቀችበት መታጠቢያ ቤት እንድትወጣ ያደረጓት ሲሆን ሽጉጥም ደግነውበታል ነበር ተብሏል።
ላቲፋ ዱባይ ከተመለሰች በኋላ ተሰውራለች። የስፖርት መምህሯ እንዲሁም ሌሎች የመርከቡ ሰራተኞች በዱባይ በቁጥጥር ስር ለሁለት ሳምንታት ከቆዩ በኋላ ነፃ ወጥተዋል።
የህንድ መንግሥት በልዕልቷ ቁጥጥር ስር መዋል የነበረው ሚናን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ከሶስት አመታት በፊት ለማምለጥ ከመሞከሯ በፊት ልዕልት ላቲፋ ዩቲዪብ ላይ የተለቀቀ አንድ ቪዲዮ ላይም "ይሄንን ቪዲዮ የምትመለከቱ ከሆነ ጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለሁም ማለት ነው። ሞቼያለሁ ወይም ክፉኛ በሆነ መጥፎ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት" የሚል ነበር።
ቪዲዮው የወጣው ከታገተችና ከታሰረች በኋላ ነበር።
ይህም ቪዲዮ ነው ልዕልቷ እንድትፈታ አለም አቀፍ ግፊቶችንና ጫናዎችን ያመጣው።












