የቀድሞው የማዕከላዊ አፍሪካ የእግር ኳስ ባለስልጣን በጦር ወንጀል ሊከሰሱ ነው

ፓትሪክ ኤድዋርድ ንጋይሶና

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፓትሪክ ኤድዋርድ ንጋይሶና

የቀድሞው የማዕከላዊ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ በጦር ወንጀል ክስ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ፊት ሊቀርቡ ነው።

ባላካ የተባለውን ቡድን የሚቃወሙ ክርስትያኖች መሪ የነበረው ፓትሪክ-ኤድዋርድ ንጋይሶና በአገሪቱ ውስጥ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ተጠርጥሮ ነው ችሎት ይቆማል የተባለው።

ፓትሪክና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ የነበረው አልፍሬድ ያካቶም በፈረንጆቹ 2013-14 በአገሪቱ ሙስሊሞች ላይ ፈፅመውታል በተባለው ወንጀል ነው የዓለም አቀፉ ጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት [አይሲሲ] የሚፈልጋቸው።

ሁለት ሦስተኛው ክፍሏ በአማፂዎች እጅ ያለው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በጦርነት እየታመሰች ትገኛለች።

የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የነበረችው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ወደ ጦርነት የገባችው አናሳ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች ሥልጣን ከያዙ በኋላ ነው።

ሴሌካ የተባሉት ሙስሊም አማፅያን በፈረንጆቹ 2013 ሥልጣን መያዛቸው ይታወሳል።

በተቃራኒው ፀረ-ባላካ የተባለው የክርስትያን አማፅያን ቡድን ፕሬዝደንት ፍራንሷ ቦዚዜ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ነው እየተስፋፋ የመጣው።

በዚህ ግጭት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱ በተጨማሪ፤ የተባበሩት መንግሥታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል ይላል።

ፓትሪክ-ኤድዋርድ ማነው?

ሰውዬው ራሱን የፀረ-ባላካ ቡድን አጋር መሪ አድርጎ የሾመው በገዛ ፈቃዱ ነው።

ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) እንደሚለው በዚህ ሥልጣኑ ወቅት እንደ ግድያ፣ ማሰቃየት እንዲሁም ሕፃናትን ለውትድርና መመልመል የመሳሰሉ የጦር ወንጀሎች ፈፅሟል።

በማዕከላዊ አፍሪካ በ2015 በተደረገው ምርጫ ላይ እንዳይሳተፍ የታገደውም በእነዚህ ወንጀሎች በመጠርጠሩ ነው።

ነገር ግን ተጠርጣሪውን እኔ ከደሙ ንፁህ ነኝ ሲል ያስተባብላል።

ግለሰቡ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ በመሆን አገልግሏል። ለአጭር ጊዜ የስፖርት ሚኒስትር ሆኖም ተሹሞ ነበር።

ከዚያ በመቀጠል በ2018 የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን [ካፍ] ውስጥም ሠርቷል። በወቅቱ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ውሳኔውን ተቃውመውት ነበር።

የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ሰውዬውን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት በፈረንጆቹ ታኅሣስ 2018 ነበር።

ጥር 2019 ላይ ደግሞ ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፎ ተሰጠ።

አልፍሬድ ያካቶም ማነው?

ራምቦ በተሰኘው ቅፅል ስሙ የሚታወቀው አልፍሬድ በግድያ፣ በማሰቃየትና ሰላማዊ ዜጎችን በማጥቃት ይጠረጠራል።

ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ግለሰቡ ሕፃናትን ለፀረ-ባላካ ቡድን በመልመል እጁ አለበት ሲል ይወነጅለዋል።

ሰውዬው ምንም ወንጀል አልፈፀምኩም ሲል ያስተባብላል።

ምንም እንኳ የተባበሩት መንግሥታት ቅጣት ቢጥልበትም በ2016 በአገሩ የሕዝብ እንደራሴ ሆኖ ተመርጦ ነበር።

በ2018 የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ ሳለ ሽጉጡን አውጥቶ ተኩሶ በማምለጡ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።

ሰውዬው ይህን ያደረገው ከአንድ ሌላ እንደራሴ ጋር በገባው ቅራኔ ምክንያት ነው።

ከማዕከላዊ አፍሪካ ለአይሲሲ ተላልፎ የተሰጠ የመጀመሪያው ተጠርጣሪም ሆኗል።

ማዕከላዊ አፍሪካ ውስጥ ምን እየተፈፀመ ነው?

ምንም እንኳ ሁለቱ ኃያላን የሚሊሻ መሪዎች በቁጥጥር ሥር ቢውሉም አሁንም አገሪቱ ከጦርነት አልወጣችም።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ቦዚዜ በ2019 ከነበረቡት ስደት ቢመለሱም ባለፈው ታኅሣስ በተካሄደው ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ ታግደው ነበር።

ፕሬዝደንት ቦዚዜ አሁን በማዕድን በበለፀገችው አገር ውስጥ ለሚስተዋለው ነውጥ ተጠያቂ ናቸው እየተባለ ነው።

ከፕሬዝደንቱ ጋር በጋራ እየሠሩ ናቸው የሚባሉ አማፅያን ቡድኖች ሰፊው የአገሪቱን ክፍል ይዘዋል። ወደ ዋና ከተማዋ ባንጉይ እየገሰገሱም ይገኛሉ።

ነገር ግን ፕሬዝደንቱ እኔ ከአማፅያኑ ጋር ግንኙነት የለኝም ሲሉ ያስተባብላሉ።

አማፅያኑ ባለፈው ታኅሣስ በተደረገው ምርጫ አሸናፊ የሆኑት ፎስቲን-አርቼንጅን አይቀበሏቸውም። ምርጫ ድጋሚ እንዲደርግም ይሻሉ።

ከሩዋንዳ፣ ፈረንሳይና ሩሲያ የተውጣጡ ከ12 ሺህ በላይ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች የአገሪቱን መንግሥት ለመደገፍ ቢገቡም ሰላማዊ ዜጎችን ከመፈናቀል አልታደጓቸውም።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት [ዩኤንኤችሲአር] ባለፈው ጥር ባወጣው መረጃ ቢያንስ 92 ሺህ ዜጎች ወደ ኮንጎ፣ 13 ሺህ ሰዎች ደግሞ ወደ ካሜሩን፣ ቻድና ኮንጎ ብራዛቪል ተሰደዋል ይላል።

የተቀሩት ደግሞ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ናቸው።