"የተማረ ወንድ አይደፍርም" ያሉት ሚኒስትር ከፍተኛ ውግዘትን አስተናገዱ

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images
"የተማረ ወንድ አይደፍርም" በማለት የተናገሩት የደቡብ አፍሪካ የትምህርት ሚኒስትር ከፍተኛ ውግዘትን እያስተናገዱ ነው ተባለ።
ሚኒስትሯ አንጂ ሞትሼክጋ ስለ ትምህርት ጠቃሚነት እያስረዱ በነበረበት ወቅት ነው ይህንን አስተያየት የሰጡት ተብሏል።
በያዝነው ሳምንት ሰኞ እለት ሚኒስትሯ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደተናገሩት ግለሰቦች በትምህርታቸው የላቀ ደረጃ ላይ ከደረሱ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች ነውረኛ ተግባራት ላይ የመሳተፍ እድላቸው አነስተኛ ነው ብለዋል።
በርካቶች የሚኒስትሯ አስተያየት መሰረታዊ የሆነውን የፆታዎች የኃይል ሚዛን ልዩነትን ያላገናዘበ ነው ሲሉ ተችተዋቸዋል።
በቦታው የነበሩት ተማሪዎች በሚኒስትሯ አስተያየት ባለመስማማት ሲያጉረመርሙ የተሰማ ሲሆን ሚኒስትሯም ለዚሁ ምላሽ በሚመስል መልኩ "የተማሩ ወንዶች በእንደዚህ አይነት ወንጀለኛ ድርጊቶች መሳተፋቸው በጣም አሳዛኝ ነው" ብለዋል።
የተወሰነ ንግግራቸው ተቀንጭቦ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጋራ ሲሆን በርካቶችንም አስቆጥቷል። የመድፈር ባህል በተንሰራባት ደቡብ አፍሪካ የተማሩ ወንዶች አይደፍሩም ምን ማለት ነው በሚልም ብዙዎች ተችተዋል።
ሚኒስትሯ በበኩላቸው አስተያየታቸው ከአውድ ውጭ እንደተወሰደ ተናግረዋል።
"መድፈር ከስልጣንና ኃይል ጋር የተገናኘ ነው። በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን የኃይል ሚዛን ልዩነት ለማስረዳት ወንዶችን ከህፃንነታቸው ጀምሮ እንዲያውቁ በማለት በትምህርተ ስርአቱ ቀርፀን እያስተማርን እንገኛለን። ወንዶች የኃይል ሚዛንን በተመለከተ፣ አባታዊ ስርአትን እንዲሁም የተሳሳተ የወንድነት ትርጉምን በተመለከተ ሊማሩ ይገባል። በተለይ ወሲባዊ ጥቃትን ለመታገል ወንዶች በፆታዎቹ መካከል ስላለው የኃይል ሚዛን ሊማሩ ይገባል" በማለት ከሚኒስትሯ የወጣው መግለጫ አስፍሯል።
በአውሮፓውያኑ 2019 ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ወሲባዊ ጥቃቶች የአገሪቱ ብሔራዊ ቀውስ ነው በማለት አውጀው ነበር።
በየአመቱም 40 ሺህ ወሲባዊ ጥቃቶች ሪፖርት የሚደረጉ ሲሆን ይህም በአገሪቷ ካለው ቁጥር አንፃር ኢምንት ነው ይላሉ።












