የቀድሞ የተመድ መልዕክተኛ በታገተችው የዱባይ ልዕልት ላይ ስህተት ፈፅመዋል ተባለ

ልእልት ላቲፋና ሜሪ ሮቢንሰን

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ መልዕክተኛና የአየርላንድ ፕረሬዚዳንት የነበሩት ሜሪ ሮቢንሰን በታገተችው የዱባይ ልዕልት ላቲፋ አል ማክቱም ላይ ትልቅ ስህተት ፈፅመዋል ተባለ።

የዱባይ መሪ ልጅ ልዕልት ላቲፋ በአውሮፓውያኑ 2018 ከአገር ጠፍታ ልትወጣ መሞከሯን ተከትሎ "የተረበሸች ወጣት ናት" ሲሉ ፈርጀዋት ነበር።

ነገር ግን ሜሪ ሮቢንሰን በቅርቡ ለቢቢሲ ፓኖራማ እንደተናገሩት በልዕልቷ ቤተሰብ በአሳዛኝ ሁኔታ መሸወዳቸውን አምነዋል።

በያዝነው ሳምንት እንዲሁ ሜሪ ሮቢንሰን አርቲኢ ለተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት "ጉዳይዋን በንቃት ልከታተለው በተገባ ነበር"ብለዋል

በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የነበሩት ሜሪ ሮቢንሰንና ልዕልት ላቲፋ በህይወት መኖሯን ለማረጋገጥ ከአራት አመታተ በፊት የተነሱት ፎቶ በርካቶች ተጋርተውታል።

መልዕክተኛዋ ከአራት አመት በፊት በዱባይ የንጉሳዊ ቤተሰብ ግብዣ መሰረት ነው ልዕልቲቷን ያገኟት።

አርቲኢ ከተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ምን ያህል ስህተት መፈፀሜን ስረዳ በጣም ነው የጎዳኝ" ብለዋል።

አክለውም "ከዚህ ቀደም ከፈፀምኳቸው ስህተቶች በሙሉ ከባዱ ይህ ነው። በእውነቱ እንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደማልገባ ተስፋ አደርጋለሁ" ማለታቸው ተዘግቧል።

የላቲፋህ አባት ሼክ መሃመድ ቢን ራሺል አል ማክቱም በአለማችን ካሉ መሪዎች አንደኛ ሃብታም ሲሆኑ ፤ የዱባይ መሪ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው።

ልዕልቲቷ አባቷ እንዳገቷትና ለህይወቷ በከፍተኛ ሁኔታም እንደምትሰጋ በቅርቡ በወጣ ሚስጥራዊ ቪዲዮ ላይ ገልፃለች።

በአሁኑ ወቅት በአንድ ቪላ ውስጥ ተዘግቶባት እንምትገኝና ነፃ አውጡኝ ስትል ተማፅናለች።

ከሶስት አመታት በፊት ከአገር ሸሽታ ልትወጣም በሞከረችበት ወቅት የጦር ኮማንዶዎች አፍነው እንደወሰዷትና በእስር ላይ እንደምትገኝ ልዕልት ላቲፋ አል ማክቱም ተናግራለች።

ሜሪ ሮቢንሰን ልዕልት ላቲፋ ያለችበት ሁኔታና ቦታ እንዲገለፅ አለማቀፋዊ ጫና እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።በተጨማሪም ከአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሞን ኮቬኔ ጋርም በልዕልቲቷ ጉዳይ እየመከሩ መሆኑን ገልፀዋል።

"በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ድርጅት ምክር ቤት ጉዳዩን እያየው ሲሆን ከዚህ ቀደምም በጄኔቫ የሚገኘው አምባሳደራችን ከተመድ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር አንዳንድ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነግረውኛል" ብለዋል።

የቀድሞ መልዕክተኛዋ ላቲፋ ፖለቲካዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት፣ በአሁኑ ወቅትም "መቶ በመቶ አምናታለሁ" እንዲሁም ነፃ ልትወጣ ይገባል ብለዋል።

የዱባይም ሆነ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም በቤተሰቦቿ እንክብካቤ ውስጥ እንደሆነችና ደህንነቷም የተጠበቀ ነው የሚል መግለጫ ሰጥተው ነበር።