በኬንያ ያሉ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በተስፋ መቁረጥና በስጋት ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያ ውስጥ በሚገኙ ዋነኛ የስደተኞች ማቆያ ካምፖች ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት በአሰቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ቆይተዋል።
በቅርቡም የኬንያ መንግሥት የካኩማና የዳደብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን እንደሚዘጋ ካስታወቀ በኋላ ሕይወታቸው ከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ መግባቱን እንዲሁም ሥነ ልቦናቸው መጎዳቱን ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ይናገራሉ።
የኬንያ መንግሥት ካምፖቹን ለመዝጋት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰጠው ቀነ ገደብ የስደተኞች ድርጅቱ ለፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ከ14 ቀን ወደ አንድ ወር ተራዝሟል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) መረጃ መሰረት እስከ የካቲት 2021 (እአአ) ድረስ በዳደብ ስደተኞች መጠለያ ውስጥ ብቻ 224 ሺህ 642 እንዲሁም ካኩማ በሚገኘው መጠለያ 206 ሺህ 458 ስደተኞች ይገኛሉ።
በአጠቃላይ በኬንያ የተለያዩ ከተሞች ከሚኖሩ ስደተኞች ጋር ሲደመር ከ 500 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች አሉ።
እነዚህ ስደተኞች ደግሞ ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከቡሩንዲ፣ ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከኡጋንዳ፣ ከሩዋንዳ እና ሌሎች አገራት የመጡ ናቸው።
ከእነዚህ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከሶማሊያ የመጡ ስደተኞች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ደግሞ ከ29 ሺህ በላይ መሆናቸውን የድርጅቱ ሰነድ ያስረዳል።
ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ
ከ27 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ የኬንያን ድንበር ተሻግረው ዳደብ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን የተናገሩት አቶ መሐመድ አብዱላሂ፣ በአሁኑ ጊዜ ካኩማ ወደሚገኘው ካሎቤ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
የኬንያ መንግሥት ባለፈው መጋቢት ወር የስደተኞች መጠለያው እንዲዘጋለት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅትን ከጠየቀ በኋላ "ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን" ይላሉ አቶ መሐመድ።
"ቀድሞውኑም ይህንን መረጃ የነገረን አልነበረም። ሊያጋጥመን ስለሚችለው ጉዳይ እና እኛን ስለሚመለከተው ይህንን መረጃ ባለመስማታችን እጅጉን ተጎድተናል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የስደተኞቹ መጠለያ ካምፖች እንዲዘጉ የኬንያ መንግሥት መወሰኑን ማንም እንዳልነገራቸው አቶ አህመድ ጠቅሰው፤ ዜናውን ከመገናኛ ብዙሃን መስማታቸውን ተናግረዋል።
"አስራ አራቱን ቀን እንዲሁ በስጋት ነው ያሳለፍነው፤ አሁን አንዱን ወር እያገባደድን ነው። የሚሆንብንን አናውቅም" ሲሉ ስጋታቸውን ያክላሉ።
ቀድሞውኑ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ችግር ጋርጦባቸው እንደነበር የሚገልፁት አቶ መሐመድ፣ አሁን ደግሞ ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ መባሉ እጅጉን አሳስቦናል ብለዋል።
"ስደተኛው ሥነ ልቦናው ተጎድቷል። ሕይወታቸውን በገዛ እጃቸው የሚያጠፉ ሰዎች አሉ። ከትናንት በስተያ እኔ በምገኝበት መጠለያ ጣብያ ካሎቤ፣ አንድ የደቡብ ሱዳን ዜጋ፣ እጅግ ከመጨነቁ የተነሳ ራሱን አጥፍቷል። ይህ ጉዳይ ብዙ ሰውን አስደንግጧል" ብለዋል አቶ መሐመድ።
"ከተስፋ መቁረጥ የተነሳ፣ ብዙዎች ራሳቸውን ወደ ማጥፋት እያመሩ ነው" የሚሉት አቶ መሐመድ፣ መጻዒ ሕይወታቸው በተስፋ መቁረጥ መሞላቱን ያስረዳሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የገጠማቸውን ተግዳሮት ሲያስረዱ "አገር ቤት ያለው ሁኔታ ያሳስበናል፤ የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት የሚያደርገው ድጋፍ አናሳ ነው። አሁን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወዲህ ደግሞ ምንም እየረዱን አይደለም፤ ቀደም ሲል ሰዉ በራሱ እየተሯሯጠ ሰርቶ ያድር ነበር። አሁን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መስራትም አይቻልም፤ ሁሉም ተስፋ ቆርጧል" ብለዋል።
"አብዛኛው ሰው አቅሉን እንደሳተ ሰው ከራሱ ጋር እያወራ ነው የሚሄደው" ሲሉ ያለውን ሁኔታ የሚገልጹት አቶ መሐመድ፣ ይህ ከፍተኛ ስጋት ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ሌላ ከዳደብ መጠለያ ጣብያ ቢቢሲ ያናገረውና ስሙ እንዳይገለፅ የጠየቀ ስደተኛ፣ የኬንያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 14 ቀናት ከሰጠ በኋላ አንድም የተቀየረ ነገር የለም ሲል ይናገራል።
"የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሥራ የጀመረ ይመስላል" ሲል የሚሰጋው ይህ ግለሰብ፣ እስካሁን ድረስ በተጨባጭ ያየው ነገር አለመኖሩን ገልጿል።
በርካታ ኬንያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ወደ ሶስተኛ አገራት ለመሻገር እየተጠባበቁ ሲሆን፣ ስደተኞቹ ወደ ሌላ አፍሪካ አገራት ሊዘዋወሩ ነው የሚል መረጃ በስፋት መናፈሱ ስጋታቸውን እንደጨመረው ይናገራል።
"ለረዥም ጊዜ ሰዉ ራሱን ያደራጀበት አገር ውጣልኝ ሲል ከዚህ በላይ ሥነ ልቦናን የሚሰብር ነገር የለም" ሲልም ሁኔታውን ይገልፀዋል።
"እዚሁ ያለንበትን ስፍራ፣ ቤታችን ቀያችን ብለን ራሳችንን አሳምነን እንኖር ነበር" የሚለው ይህ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ግለሰብ፣ ቤተሰብ መመስረታቸውን እና "በአንድ ቅጽበት መንግሥት ተነሱ ውጡልኝ ሲል ጉዳቱ ይከፋል" ብሏል።
ሰዉ ሁሉ በሄደበት ቦታ ሁሉ የኬንያ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ምን እንደሚወስኑ ነው የሚጠያየቀው፣ ስጋቱን ከራሱ ጋር እያወራ ይሄዳል በማለት "የእብደት ስሜት ውስጥ እየተገባ ነው" ሲል ይገልጻል።
በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚኖረው እድሪስ ከአገር ከወጣ 45 ዓመት እንደሆነው ይናገራል።
እድሪስ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እኤአ በ2017 ከተመዘገቡ ስደተኞች መካከል አንዱ ነው። "አሁንም ተመሳሳይ ሂደት ላይ ነን" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ሂዱ ከማለት ውጪ፣ የት እና በምን እንደምንጓዝ አቅጣጫ ያመላከተን አካል የለም" ይላል።
ከዳዳብ ወደ ካኩማ አስገድደው ነው የሚወስዱት የሚለው እድሪስ "እኛ አንሄድም ብለን እምቢ አለን፤ አስገድደው ሊወስዱን ሲሉ እዚያ ሄደን ከምንቸገር ወደ አገራችን እንመለሳለን አልን። እስካሁን ሁኔታዎችን አላመቻቹልንም" በማለት ያለበትን ሁኔታ ያስረዳል።
የኬንያ መንግሥት የመጠለያ ጣቢያዎቹ ስለመዘጋታቸው ካስታወቀ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳላችሁ የሚል ወሬ እንዳለ እድሪስ ይናገራል።
"ነገር ግን ለመሄድ በምንጠይቅበት ጊዜ ሂዱ ከማለት ውጪ የሚያማክረንም ሆነ አስፈላጊውን ነገር የሚያመቻችልን አካል አላገኘንም። ነገር ግን በግንቦት ወር መግቢያ ላይ የመጀመሪያው ዙር ሰዎችን መመለስ ይጀምራል ብለውናል። ከባድ ችግር ውስጥ ነን" ይላል።
ኬንያ ውስጥ በሚገኙት ትላልቆቹ የስደኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገራት ስደተኞች ለዓመታት ወደ ሦስተኛ አገር ለመጓዝ ሲጠባበቁ ቆይተዋል።
በተለያዩ ጊዜያትም የኬንያ መንግሥት እነዚህን የስደተኞች መጠለያዎች እንደሚዘጋ ሲገልጽ የቆ ሲሆን በዚህ ዓመትም ባለፈው ወር ካምፖቹን እንደሚዘጋና የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም ለስደተኞቹ መፍትሔ እንዲፈልግ ጠይቋል።













