ሱፐር ሊግ፡ 'ታላላቆቹ ስድስት' የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ቶተንሀም በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ተስማሙ።
የአውሮፓ እግር ኳስን ባልተጠበቀ መልኩ የነቀነቀው ይህ ውሳኔ በርካቶችን ያስገረመ ሲሆን ከጣልያን ኤሲ ሚላን፣ ኢንተር ሚላን እና ጁቬንቱስ በሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ወስነዋል። ከስፔን ደግሞ ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ይቀላቀላሉ።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንደገለጸው መስራች ቡድኖቹ የሳምንቱ ግማሽ ላይ ጨዋታዎቹን ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን የአገራቸው ሊግ ጨዋታ ላይ ግን መሳተፋቸውን አያቆሙም።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ አክሎም' "እቅዱ ተግባራዊ መደረግ ሲችል የመጀመሪያው የውድድር ዓመት ወዲያውኑ ይጀመራል። ሶስት ተጨማሪ ቡድኖች ደግሞ ሊጉን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል'' ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የወንዶቹ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ከተጀመረ በኋላ የሴቶች ሱፐር ሊግም እንደሚጀመር ተገልጿል።
እሁድ ዕለት የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የዩናይትግ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውሳኔውን አውግዘውታል።
የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪው ፊፋ በበኩሉ ቀደም ብሎ ለመሰል ውድድሮች እውቅና እንደማይሰጥና በውድድሩ የሚሳተፉ ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫ ላይ ላይሳተፉ እንደሚችሉ አስታውቋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ዜና ከተሰማ በኋላ ፊፋ "ለእግር ኳስ ሲባል በዚህ ውሳኔ ላይ የተሳተፉት አካላት በሙል የተረጋጋ፣ ጠቃሚና ሁሉንም የሚጠቅም ውይይት ሊያደርጉ ይገባል" ብሏል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርም ትናንት ባወጣው መግለጫ በአውሮፓ ሱፐር ሊግ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ከሁሉም የአገር ውስጥ ውድድሮች ሊታገዱ እንደሚችሉ ያስታወቀ ሲሆን በአውሮፓም ሆነ በዓለም መድረክ ከብሔራዊ ቡድን ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ደግሞ በመግለጫው "ወደፊት መስራች ክለቦቹ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና ፊፋ ጋር አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ያደርጋሉ'' ብሏል።
ሊጉ 20 ተሳታፊ ብድኖችን የሚያካትት ሲሆን 12ቱ መስራች ክለቦች እና እስካሁን ስማቸው ያልተጠቀሰው ሶስት ክለቦች በፍጥነት ይቀላቀላሉ። ከአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች ደግሞ አምስት ቡድኖች ተወዳድረው የአውሮፓ ሱፐር ሊግን ይቀላቀላሉ።
በእቅዱ መሰረት የአውሮፓ ሱፐር ሊግ በየዓመቱ ነሀሴ ወር ላይ የሚመጅር ሲሆን ጨዋታዎቹም የሳምንቱ አጋማሽ ላይ ይደረጋሉ። ተሳታፊዎቹ 20 ቡድኖችም በሁለት ምድቦች ተከፍለው በደርሶ መልስ ጨዋታ ይፋለማሉ።
ከሁለቱ ምድቦች ከአንድ እስከ ሶስት ሆነው የሚጨርሱት ቡድኖች ለእሩብ ፍጻሜ የሚያልፉ ሲሆን አራተኛና አምስተኛዎቹ ደግሞ እርስ በርስ ተጋጥመው አሸናፊው እሩብ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንደሚለው ይህ ውድድር ከአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ በተሻ መልኩ ገንዘብ የሚያስገኝ ሲሆን ተሳታፊ ክለቦችም ጠቀም ያለ ትርፍ ያገኙበታል።












