ሩስያ 20 የቼክ ሪፐብሊክ ዲፕሎማቶችን አባረረች

የሩሲያ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ቼክ ሪፐብሊክ ባለፈው ቅዳሜ 18 የሩስያ ዲፕሎማቶችን ማባረሯን ተከትሎ ሩሲያ በአጸፋው 20 የቼክ ሪፓብሊክ ዲፕሎማቶችን አባረርች።

የቼክ ደህንነት ሰዎች እንደሚሉት የተባረሩት ሩስያዊያን ዲፕሎማቶች በድብቅ የስለላ ሥራ የሚሠሩ ናቸው።

ቼክ ሪፐብሊክ ሰዎቹን ያባረረቻቸው በፈረንጆቹ 2014 በአንድ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ዴፖ ላይ በደረሰ ፍንዳታ ላይ እጃቸው አለበት በሚል ነው።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰኞ ዕለት ስለ ጉዳዩ እንደሚመክሩ ተነግሯል።

ሩስያ የቼክ ሪብሊክ ዲፕሎማቶች በአንድ ቀን ሞስኮን ጥለው እንዲወጡ ያዘዘች ሲሆን ቼክ ሪፐብሊክ ደግሞ 72 ሰዓታት ሰጥታለች።

የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቼክን ውሳኔ "ያልተጠበቀ" እንዲሁም "ጠብ አጫሪ" ብሎታል።

"በቅርቡ ሩስያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስን ለማስደሰት ካላቸው ፍላጎት አንፃር ነው የቼክ ባለሥልጣናት ይህን ድርጊት የፈፀሙት" ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በለቀቀው መግለጫ።

የተከሰተው ምንድነው?

የቼክ ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሩስያ ዲፕሎማቶች የደህንነት ሰዎች ናቸው። ሩስያ ደግሞ ይህ ክስ መሠረት አልባና ግራ አጋቢ ነው ትላለች።

በፈረንጆቹ ጥቅምት 2014 ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ ካለ አንድ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ላይ የደረሰው ፍንዳታ ማከማቻውን ከጥቅም ውጭ አድርጎት ነበር።

ቭርቢቲች ጫካ ውስጥ የነበረው ማከማቻ ላይ የደረሰው ፍንዳታ በአቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎችን መኖሪያ መስኮት መስታወት ሰባብሮ ነበር።

ማከማቻው ውስጥ ይሠሩ የነበሩ አንድ የ56 ዓመት ግለሰብና ሌላ የ69 ዓመት ሰው ሬሣ ከአንድ ወር በኋላ በሥፍራው መገኘቱ ይታወሳል።

በወቅቱ ፍንዳታው ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሳይሆን አደጋ ነው ተብሎ ነበር።

ነገር ግን የቼክ ሪፐብሊክ ባለሥልጣናት ምርመራ ካደረጉ በኋላ ጣታቸውን ሩስያ ላይ ጠቁመዋል።

የቼክ ፖሊስ አሌክሳንደር ሚሽኪን እና አናቶሊ ቼፒጎቭ የተባሉት ሁለት ሩስያዊያንን በፍንዳታው እጃቸው አለበት በሚል ማንነታቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።

ፖሊስ ይህን ያለው ማከማቻውን ያስተዳድር ከነበረው አይሜክ ግሩፕ ኢሜይል ውስጥ የሁለቱ ሰዎች የፓስፖርት ፎቶ በመገኘቱ ነው።

ፓስፖርት
የምስሉ መግለጫ, በኢሜይል መልዕክቱ ውስጥ የሁለቱ ሰዎች የፓስፖርት ፎቶ ተገኝቷል።

ኢሜይሉ ሁለቱ ሰዎች ፈቃድ እንዲሰጣቸውና በማከማቻው ተገኝተው ምርመራ እንዲያደርጉ ይጠይቃል። ሰዎቹ በዚህ ኢሜይል ላይ ስማቸውና ዜግነታቸው ተቀይሮ ነው የቀረበው።

ሁለቱ ግለሰቦቹ እንግሊዝ ውስጥ አንድ የቀድሞ የሩስያ ሰላይን በመመረዝ ተጠርጥረው ነበር።

ቼክ ሪፐብሊክ ክሳቸውን ለአውሮፓ ሕብረትና ለኔቶ ለማቅረብ ተሰናድተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቼክ ሪብሊክ ጎን እንደሚቆም አስታውቋል። አሜሪካ በቅርቡ ሩስያ ላይ ማዕቀብ መጣሏና 10 ሩስያዊያን ዲፕሎማቶች ሃገሯን ጥለው እንዲወጡ ማዘዟ አይዘነጋም።