አዲስ አበባ ውስጥ የእጅ ቦምብ ፈንድቶ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ

የአዲስ አበባ ፖሊስ አርማ

የፎቶው ባለመብት, AA POLICE

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባልታወቀ ሁኔታ የፈነዳ የእጅ ቦምብ የሁለት ሰዎች ህይወት መቅጠፉን እና አንድ ሰው ደግሞ መቁሰሉን ፖሊስ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘውና ሜትሮሎጂ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በፈነዳው የእጅ ቦምብ የሁለት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉንና አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ክፉኛ መቁሰሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ ፍንዳታውን ተከትሎ አደጋው ባጋጠመበት ስፍራ ላይ ከአንደኛው ሟች ኪስ ውስጥ ተጨማሪ ያልፈነዳ የእጅ ቦንብ ማግኘቱን አስታውቋል።

ለሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው ፍንዳታ ያጋጠመው እሁድ ሚያዝያ 10/2013 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተባለው ስፍራ ለልማት በተዘጋጀ ቦታ ላይ እንደሆነ ፖሊስ አመልክቷል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መርማሪ ረዳት ኢንስፔክተር ዳንኤል ታፈሰ ስለተከሰተው ፍንዳታ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን፣ አንድ ግለሰብ ሁለት ሴቶች ጋር ለልማት ወደታጠረው ስፍራ ከገባ በኋላ ፍንዳታ መከሰቱን ገልጸዋል።

ለሁለት ሰዎች ሞትና ለአንድ ሰው መቁሰል ምክንያት የሆነው አደጋን ተከትሎ የአዲስ አበባና የፌደራል ፖሊስ የቴክኒክና የፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎች በአደጋው ስፍራ ተገኝተው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ አካባቢውን ከእንቅስቃሴ ነጻ በማድረግ ምርመራ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ፖሊስ ስለተከሰተው የቦምብ ፍንዳታና ምክንያቱ እንዲሁም በክስተቱ ህይወታቸው ስላለፈው ሰዎች ማንነት ለማወቅ ምርመራ እያካሄደ መሆኑ ተገልጿል።