በጦርነት ስትታመስ የከረመችው ሶሪያ ምርጫ ልታካሂድ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችው ሶሪያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ልታካሂድ መሆኑን አስታወቀች።
የአገሪቱ ፓርላማ በቀጣዩ ወር የአገሪቱን ፕሬዘዳንት ለመምረጥ የሚያስችል ምርጫ እንደሚካሄድ ይፋ አድርጓል።
ይህም የፕሬዳንት በሽር አል አሳድ ስልጣንን ለቀጣይ ሰባት ዓመታ ለማረጋገጥ የታሰበ ሳይሆን እንደማይቀር ተነግሯል።
ከ 10 ዓመታ በላይ የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጠለበት እና የኢኮኖሚ ቀውሱም ባየለበት በዚህ ወቅት አሳድ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም።
በአሳድ የሚመራው የሶርያ መንግሥት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያለባቸውን አካባቢዎች ተቆጣጥሮ ይገኛል። በ 10 ዓመቱ ጦርነት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ የሶሪያ ግማሽ የሚሆነው ህዝብም አገር ለቆ ተሰዷል።
ከአንድ ወር በኃላ የሚካሄደው ይህ ምርጫም ለመጪው ሰባት ዓመታት ሶሪያን የሚመራውን ፕሬዘዳንት የሚመረጥበት እንደሚሆን ተገልጿል።
ከዛሬ ጀምሮ ከፕሬዘዳንቱ ጋር የሚወዳደሩ እጩዎች መመዝገብ ይጀምራል።
በመላው አለም ያሉ ሶሪያዊያንም ከምርጫው እለት ስድስት ቀናት ቀደም ብለው ኤምባሲ በመሄድ ለመራጭነት መመዝገብ ይችላሉ ተብሏል።
ይህ ምርጫም የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የሚደረግ ሁለተኛ ምርጫ ነው። እኤአ በ 2014 የተካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ብሎም ህገ ወጥ በሚል በተቃዋሚዎች እዲሁም በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት ውድቅ የተደረገ ነበር። በዚህ ምርጫ አሳድ 92 በመቶ ድምፅ በማግኘት ነበር አሸንፊያለሁ ያሉት።
ይህ ምርጫ ከአስርተ አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ከአሳድ ቤተሰብ ውጪ ያለ ሰው እንዲወዳደር የተፈቀደበት ምርጫ የነበረ ሲሆን ሁለቱ ተፎካካሪዎች ግን እምብዛም የማይታወቁ ነበሩ።












