በሲሪላንካ የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋ መድረክ ላይ በተፈጠረ ጠብ ተጎዳች

ወ/ት ስሪላንካ ትዳሯን የፈታች ናት በሚል ጠቡ መነሳቱ ታውቋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የስሪላንካ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ በመድረክ ላይ በተፈጠረ ጠብ መጎዳቷ ተነገረ።

እሁድ እለት ፑሽፒካ ዴ ሲልቫ ወይዘሪት ስሪላንካ በመሆን ማሸነፏ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ነበር የተገለፀው።

ከደቂቃዎች በኋላ የ2019 አሸናፊ የሆነችው ወይዘሪት ዴ ሲልቫ፣ የአሸናፊነት ዘውዱን የዚህ ዓመት አሸናፊዋ ትዳሯን የፈታች በመሆኗ ለእርሷ አላጠልቅም በማለቷ ጠብ ተፈጥሯል።

የውድድሩ ዳኞች ዴ ሲልቫ ትዳሯን የፈታች አለመሆኗን ካረጋገጡ በኋላ ሽልማቱ እንዲሰጣት መደረጉ ታውቋል።

የቁንጅና ውድድር ዳኞች ዴ ሲልቫን የ2021 ወይዘሪት ስሪላንካ በማለት አሸናፊ ያደረጓት በዋና ከተማዋ ኮሎምቦ በሚገኝ ቴአትር ቤት በተካሄደ ዝግጅት ነበር።

ነገር ግን የ2019 አሸናፊዋ ካሮላይን ጁሪ፣ የቁንጅና ተወዳዳሪዎች ያገቡ እንጂ የፈቱ መሆን የለባቸውም የሚለውን ሕግ በመጥቀስ የወይዘሪት ዴ ሲልቫን ዘውድ ነጥቃለች።

"ያገቡ እና የፈቱ ሴቶችን በሚመለከት የተቀመጠ ሕግ አለ፤ ስለዚህ የቁንጅና አሸናፊዋ ዘውድ ሁለተኛ ለወጣችው ይገባል" ስትል በስፍራው ለተገኘው ታዳሚ ተናግራለች።

ከዚያም ዘውዱን ሁለተኛ ለወጣችው ተወዳዳሪ ያጠለቀችላት ሲሆን ወይዘሪት ዴ ሲልቫ መድረኩን እያለቀሰች ለቃ ወጥታለች።

የውድድሩ አዘጋጆች ወ/ት ዴ ሲልቫን ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን ትዳሯን ፈትታ ሳይሆን ተለያይታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ወ/ት ዴ ሲልቫ ከጠቡ በኋላ ጭንቅላቷ ላይ ጉዳት በመድረሱ ለመታከም ወደ ሆስፒታል መሄዷን በፌስቡክ ገጿ ላይ አስፍራለች።

"ትዳሬን የፈታሁ ሴት አይደለሁም" ስትል የጻፈችው ዴ ሲልቫ፤ "እውነተኛ ንግሥት የሌላ ሴትን ዘውድ የምትነጥቅ ሳይሆን በምስጢር ለሌላ ሴት ዘውድ የምትጭን ናት" ብላለች።

የወ/ት ስሪላንካ አዘጋጅ የሆኑት ዳይሬክተር ቻንዲማል ጄያሲንግሄ ለቢቢሲ እንዳሉት የአሸናፊነት ዘውዱ ለወ/ት ዴ ሲልቫ ማክሰኞ እለት ይመለሳል።

"አዝነናል" ያሉት ዳይሬክተሩ "ለእኛ በጣም አሳፋሪ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ወ/ሪት ስሪላንካ በአገሪቱ ከሚካሄዱ ውድድሮች ትልቁ ነው።

በበዓሉ ላይ እንግዶች ከነበሩት መካከል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ይገኙበታል።