በጎሳዎች ግጭት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ሱዳን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገች

የፎቶው ባለመብት, AFP
በምዕራብ ዳርፉር ውስጥ በተከሰተ የጎሳ ግጭት ከአርባ በላይ ሰዎች ተገድለው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተፈናቀሉ በኋላ ሱዳን በግዛቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገች።
ቅዳሜ ዕለት ኤል ጄኒና በተባለችው ከተማ በአረቦችና አረብ ባልሆኑት ማሳሊት በተባሉት ጎሳዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ 40 ሰዎች ሲገደሉ ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ጉዳዮች ተቋም (ኦቻ) እንዳለው ትናንት ሰኞ ከሰዓት በኋላም ከከተማዋ አቅራቢያ ካሉ ስፍራዎች የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።
ጨምሮም ግጭት ውስጥ የገቡት ማኅበረሰቦች ለተጨማሪ ግጭት ኃይሎቻቸውን እያሰባሰቡ በመሆናቸው በከተማዋ ውስጥ ያለው ሁኔታ አሁንም ውጥረት እንዳጠላበት ነው።
በአካባቢው ያለው የደኅንነት ሁኔታ እስኪሻሻል ድረስ ተቋሙ የሚያካሂደው የሰብአዊ እርዳታ ሥራውን ያቋረጠ ሲሆን ወደ ሥፍራው የሚደረጉ የእርዳታ በረራዎች ተሰርዘዋል።
ግጭቱ የተከሰተባት ከተማ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚጠብቁ የአካባቢው ነዋሪዎች የእርዳታ አቅርቦት ማዕከል ስትሆን በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ለችግር እንደሚዳረጉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።
ባለፈው ጥር ወር በተመሳሳይ በማሳሊትና በአረብ ማኅበረሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት ቢያንስ 129 ሰዎች ሲገደሉ ከ108 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገደው ነበር።
አብዛኞቹ ተፈናቃዮቹም በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።












