ኮሮናቫይረስ፡ በፓሪስ በድብቅ የተከወኑ 'ቅንጡ የእራት ፕሮግራሞች' ላይ ፓሊስ ምርመራ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፓሪስ በድብቅ የተከወኑ 'ቅንጡ የእራት ፕሮግራሞች' ላይ ፓሊስ ምርመራ ጀመረ
በፈረንሳይ የኮቮድ 19 ክልከላን ጥሶ ሲከናወን የነበረ የእራት መርሃ ግብር በድብቅ ተቀርፆ በአንድ የቴሌቪዥን ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ የሀገሪቱ ፓሊስ ምርመራ ጀምሯል።
ምርመራው እንዲጀመር ያዘዙት የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን ከኮቪድ 19 መከላከል መመሪያዎች በተፃራሪ የሚደረጉ ይህን መሰል መሰባሰቦች "ፍፁም ተቀባይነት የላቸውም" ብለዋል።
በፈረንሳይ የሚገኝ ኤም 6 የተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ በትዊተር ገፁ ያሰፈረው በድብቅ የተቀረፀው ቪዲዮ "ሻምፓኝ፣ ካቪያር፣ አሉ በተባሉ ሼፎች የተዘጋጁ የምግብ ዝርዝሮችና ጭምብል የሌለበት" በሚልም ማብራሪያ ነው ፊልሙን ያሳየው።
ፈረንሳይ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበር የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች። ይህ ገደብ በሀገሪቱ ሲጣል ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ዕሁድ ለ'ት ወደ ፅኑ ህሙማን ማቆያ ክፍል የገቡ ሰዎች ቁጥር 5,341 መደረሱን ተከትሎ ሆስፒታሎች በከፍተኛ ጫና ላይ ወደቀዋል።
ትምህርት ቤቶችና አንገብጋቢ ጉዳዮችን ከሚያስተናግዱ አገልግሎቶች በስተቀር የንግድ ተቋማት በሙሉ ተዘግተዋል። በምሽት የሚተገበር የሰዓት እላፊ ገደብም ተጥሏል።
በዚህ ክልከላ መሀል የተከወነ ውድ የእራት መርሃግብርን የሚያሳየው የኤም 6 ቲቪ ቪዲዮ ተሳታፊዎች ማስክ እንዳያደረጉ ሲነገራቸው ይደመጣል።
አንዱ አሳላፊ ቪዲዮን ለሚቀርፀው ጋዜጠኛ " እዚህ የሚመጡ ሰዎች ጭምብል አያጠልቁም። አንዴ እዚህ ከገባህ ኮሮና የለም" ሲለው ይሰማል።
እናም የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ይህ ቪዲዮ እውነትነቱ ከተረጋገጠ ሰዎቹ መከሰስ አለባቸው። እንደማስበው ይህንን መርሃ ግብር በማዘጋጀታቸው ሊፈረድባቸው ይገባል" ብለዋል።












