ፕሮፌሰር ሂሩት ለአፍሪካ ሕብረት የኮሚሽነርነት ቦታ ለምን ሳይመረጡ ቀሩ?

የፎቶው ባለመብት, HIRUT WOLDEMARIAM/FB
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንትነት እስከ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴርነት ድረስ ያገለገሉት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማሪያም በአፍሪካ ሕብረት የትምህርት እና የሳይንስ ጉዳዮችን ለመሚመለከተው ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ሳይመረጡ ቀርተዋል።
ለዚህም እንደ ምክንያት ከተቀመጡት ጉዳዮች መካከል በያዝነው ዓመት መተግበር የጀመረው እና በየሩዋንዳው ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ መሪነት ሲዘጋጅ የነበረው የኮሚሽኑ አዲስ መዋቅር መፅደቁ ነው።
ካጋሜ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሆነው ባገለገሉበት አንድ ዓመት ማለትም ከፈረንጆቹ 2018 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ሕብረቱ ውጤታማ አልነበረም በሚል አዳዲስ የለውጥ ሃሳቦችን አቅርበው ነበር።
ይህንን ተከትሎም ባዋቀሩት ኮሚቴ በኩል ሕብረቱን ሙሉ ለሙሉ ኦዲት ያስረደረጉ ሲሆን የሥራ ድግግሞሽን ማስቀረት ብሎም የፋይናንስ ጥገኝነትን ማስቀረት የዚሁ ለውጥ ዋና አላማዎች ነበሩ።
በፖል ካጋሜ የተመራው ይህ የለውጥ ሃሳብ ካነገባቸው አራት አላማዎች አንዱ የነበረው የሕብረቱን መዋቅር በሰብሰብ እና ውጤታማነቱን መጨመር ይገኝበታል።
በዚህ መሰረትም ሲጠና የቆየው አዲሱ መዋቅር ከዚህ ቀደም ስምንት የነበረውን የኮሚሽነሮች ቁጥር ወደ ስድስት ቀንሷል።
በ34ኛው መደበኛ የመሪዎች ጉባኤው ላይም በመጀመሪያው ቀን ምርጫ ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ኮሚሽነር እና ስድስት የዘርፍ ኮሚሽነሮችን ለመምረጥ ነበር እቅድ የተያዘው።
በሕብረቱ ታሪክ የመጀመሪያ በተባለለት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪን ለሁለተኛ ግዜ የመረጠው ጉባኤው ከሩዋንዳ የመጡትን የ ዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ ደግሞ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ኮሚሽነር አድርጎ መርጧል።
የሩዋንዳዋ ተወካይ የመጀመሪያዋ የኮሚሽኑ ሴት ምክትል ኮሚሽነር ሆነው የተመረጡ ሲሆን ይህም ፕሮፌሰር ሂሩትን በተዘዋዋሪ ከውድድር ውጪ አደርጓቸዋል።
ከፕሮ. ሂሩት ጋር እነማን ተወዳደሩ
በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ የኮሚሸነሮች ምርጫ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተያዘው ዓመት ሊስተጓጎል ይችላል የሚሉ ስጋቶች ቢኖሩም ከስድስቱ ኮሚሽነሮች አራቱን በመምረጥ ተገባዷል።
ዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዕጩ የቀረበበትም ነበር።
የኮሚሽነሮች ምርጫ በአህጉሩ ካሉ አምስት ቀጠናዎች ተመጣጥኖ እንዲመረጥ ይደረጋል። ስለዚህም ተመራጭ ኮሚሽነሮቹ ካላቸው ብቃት በሻገር የቀጠና ምጣኔም ዋና ግብአት ነው። የሕብረቱ አምስቱ ቀጠናዎች የምሥራቅ፣ የምዕራብ፣ የደቡብ፣ የሰሜን እና የማዕከላዊ ናቸው።
ፕሮፌሰር ሂሩትን ጨምሮ አምስት ተፎካካሪዎ የቀረቡበት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የኢኖቬሽን ኮሚሽነርነት ዘርፍ ከፍተኛ ዕጩ የቀረበበት ነበር።
ከምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ብቻ ሦስት ተፎካካሪዎችን ይዞ የመጣ ሲሆን ከኡጋንዳ እና ሞሪሺየስም ተወዳዳሪዎች የነበሩበት ነው።
ሪታ ታግዊራ ሞርሺየስን ወክለው የቀረቡ ሲሆን ጆን ፓትሪክ ካባዮ ደግሞ ከኡጋንዳ ከፕሮ. ሂሩት ጋር ተፎካካረዋል። በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ እና ዚምቧብዌ ተፎካካሪዎችን አቅርበዋል።
ከአፍሪካ ሕብረት ጋር የተገናኘ ሰፊ የሥራ ልምድ ያላቸው አንድ የቢቢሲ ምንጭ እንደሚገልጹት አንድ ቀጠና ሦስት ሰው ማቅረቡ በራሱ በአገራቱ መካከል ያለውን ከፍተኛ ያለመናበብ የሚያሳይ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, HIRUT/SM
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና
የሩዋንዳዋ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጥ ከውድድር ውጪ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ፍርሃት እንዳላቸው ፕሮ. ሂሩት ከኢትዮጵያ ቴሌቪሽን ጋር ጥር 22/2013 ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ገልፀው ነበር።
"ስለቀጣዩ የምርጫ ደረጃ የሰማሁት ነገር ትንሽ ግራ አጋቢ ነው ነው። የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ወይም ምክትል ከምሥራቅ አፍሪካ የሚመጣ ከሆነ ሌላ ኮሚሸነር ከቀጠናው እንደማይቀበሉ ነው። ይህ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ነው። ግን ያው በተስፋ እጠብቃለሁ" ሲሉ ሂሩት ገልፀው ነበር።
የዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው "ሳይታለም የተፈታ" እንደነበረ የምርጫ ሂደቱን በቅርበት የተከታተሉት ምንጫችን ያስረዳሉ።
ይህም ሞኒክ የሩዋንዳ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት በተለይም የአገሪቷን የንግድ አመቺነት ደረጃ ከፍ ማድረግ መቻላቸውን ጨምሮ በርካታ ስኬት ያስመዘገቡ በመሆናቸው ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው መሆኑ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት እያካሄደ ካለው ራሱን በፋይናንስ የመቻል እቅድ ጋር ተያያዞ የሞኒክ መመረጥ የሚጠበቅ ነው ሲሉ የቢቢሲ ምንጭ ያስረዳሉ።
እንዲሁም ከሃርቫርድ ኬኔዲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ከተለያዩ በዓለም ላይ ታዋቂ በሆኑ የኢኮሚክስ ትምርት ቤቶች መማራቸው ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ ብልጫ እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑንም ጨምረው ይገልፃሉ።
ሞኒክ የተወዳደሩበት ዘርፍም ቢሆን ሙሉ በሙሉ የምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪዎች የቀረቡበት ነበር። የሩዋንዳ፣ የሶማሊያ እና የኡጋንዳ ተወዳዳሪዎችን በመብለጥ ነው የተመረጡት።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን የያዘው ይህ ቀጠና ባለመናበብ እና እርስ በእርስ መግባባት ያለመቻሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ታይቷል ሲሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት ለሕብረቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያስረዳሉ።
ይህ በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጂቡቲ እና በኬንያ መካከል የነበረው ፍጥጫም ማሳያ እንደነበረ ይናገራሉ።
ሌሎች አገራት ወደ ምርጫው ከመግባታቸው በፊት በሚያካሂዱት ድርድር ቀጣናቸውን የሚወክል ሰው ለተለያዩ ምርጫዎች የሚያቀርቡ ሲሆን በተለይም የደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና በዚህ የሚታወቅ ነው ይላሉ ባለሞያዎቹ።
ፕሮ. ሂሩት የተወዳደሩበትን ዘርፍ ጨምሮ ቀሪ ሁለት የኮሚሽነሮች ምርጫ በመጪው ክረምት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ እንደሚመረጡ ይጠበቃል።
የሁለቱ ኮሚሽነሮች ምርጫ በድጋሚ በሚካሄድበት ጊዜም ሂሩትን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ ኮታ በመሙላቱ በድጋሚ መወዳደር አይችሉም።
ስለ ፕሮፌሰር ሂሩት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "በካቢኔዬ ውስጥ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትር የነበሩትና አሁን ደግሞ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሆኑት ፕሮፌ. ሂሩት ለቦታው ተገቢ ዕጩ ናቸው" ሲሉ የፕሮፌሰር ሂሩትን ዕጩነት ደግፈው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈው ነበር።
በተጨማሪም "እንደ ምሁር፣ ሳይንቲስት፣ የለውጥ መሪ እና የዲፕሎሲ ቡድን መሪነት የተለያየ ልምድ ያላቸው ሂሩት ለዚህ ቦታ ተገቢው ሰው ያደርጋቸዋል" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲመረጡ ቀስቅሰውላቸዋል።
"በአካዳሚው ዘርፍ ከፍተኛውን ማዕረግ ያገኙት ሂሩት በሦስት የተለያዩ የሚኒስትርነት ኃላፊነት ሾመናቸው አገልግለዋል" ሲሉም ስለፖለቲካዊ ተሳትፏቸው አቶ ደመቀ ገልጸው ነበር።
ፓን አፍሪካኒዝምን በአፍሪካ የትምህር ሥርዓት ውስጥ ማካተት፣ ጠንካራ የፓን አፍሪካ የትምህርት ዕድል ፕሮግራሞች መክፈት፣ በአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተጣጣመ እና እንደ አውሮፓው ኤራስ መስሙንደስ ያለ የእውቅና ሥርዓት መጣጣም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ መሪ የሆኑ የልህቀት ማዕከላትን ማቋቋም ዋና አላማዎቼ ናቸው ሲሉ ሂሩት ለመመረጥ ሃሳብ አቅርበው ነበር።
ሂሩት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መስራች ሚኒስቴር ናቸው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በሚመሩበት ወቅትም በተለይም ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ታግተው እስካሁን ያሉበት የማይታወቁ ተማሪዎች ጉዳይን በተመለከተ ትችት የሰነዘርባቸው ነበር።
ቢቢሲ ለሳምንታት ከፕሮፌሰር ሂሩት አስተያየታቸውን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ጉዳዩን የያዘው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሆነ በመግለፅ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሂሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲን በመወከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።












