የሩሲያ ዲፕሎማቶች ጓዛቸውን በእጅ በሚገፋ ጋሪ ሸክፈው ከሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ ተሻገሩ

የፎቶው ባለመብት, RUSSIAN FOREIGN MINISTRY
ሰሜን ኮሪያ በምትተገብረው ጥብቅ የኮቪዲ-19 መመሪያ ምክንያት አንድ የሩስያ ዲፕሎማቶች ቡድንና ቤተሰቦቻቸው ከሰሜን ኮሪያ ባልተለመደ ሁናቴ ለመውጣት ተገደዋል።
የዲፕሎማቶቹ ቡድን ጓዛቸውን በእጅ በሚገፋ ጋሪ ሸክፈው ከሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ ድንበር ተሻግረዋል።
ቁጥራቸው ስምንት የሚሆኑት ዲፕሎማቶቹና ቤተሰቦቻቸው ለ1 ኪ.ሜ ያክል በባቡር ሀዲድ ላይ በሚሽከረከር የእጅ ጋሪ ንብረቶቻቸውን እና ልጆቻቸውን ጭነው ወደ ሩሲያን ድንበር አቋርጠዋል። ሩሲያዊያኑ ወደ አገራቸው ድንበር ከመሻገራቸው በፊት፤ ወደ ሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር ለመድረስ ረዥም የባቡር እና የአውቶብስ ጉዞ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።
ሰሜን ኮሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በርካታ የትራንስፖርት አማራጮችን ዝግ አድርጋለች።
አገሪቱ በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጥ አንድም ሰው የለም የምትል ቢሆንም ይህንን ዕውነታ የሚጠራጠሩ ግን ባርካቶች ናቸው።
ከባለፈው ዓመት መግቢያ ጀምሮ ወደ ሰሜን ኮሪያ ባቡሮች መግባትም ሆነ መውጣት እንዳይችሉ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል። በርከት ያሉ ዓለም አቀፍ የመንገደኞች በረራም ቆሟል።
ታዲያ በዚህ መሀል ነው የሩሲያ ዲፕሎማቶች የነበራቸውን ጠባብ አማረጭ የተጠቀሙትና ያልተለመደ ጉዞ በማድረግ ከሰሜን ኮሪያ የወጡት።
"ድንበሩ ከአንድ ዓመት በላይ በመዘጋቱና የመንገደኞች እንቅስቃሴ በመቆሙ ወደ ሀገር ለመመለስ የተደረገው ጉዞ ረጅምና አድካሚ ነበር" ሲል የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገፁ ገልጿል።












