ታዋቂው የግሪክ ተዋናይ ታዳጊ በመድፈር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋለ

ዲሚትሪስ ሊግናዲስ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

.ታዋቂው የግሪክ ተዋናይና ዳይሬክተር ዲሚትሪስ ሊግናዲስ ሁለት ታዳጊ ልጆችን ደፍሯል በሚል ክስ በቁጥጥር ስር ዋለ።

የ56 አመቱ ስመ ጥር ተዋናይ የ14 አመት ወንድ ደፍሯል የተባለው በአውሮፓውያኑ 2010 ሲሆን ሁለተኛውን ክስ አስመልክቶ ዝርዝሩ ለህዝብ ይፋ አልተደረገም።

የግሪክ ብሔራዊ ቲያትር የቀድሞ ዳይሬክተር ዲሚትሪስ የተጠረጠረባቸውን የመድፈር ወንጀሎች አልፈፀምኩም እንዳለም ጠበቃው አሳውቀዋል።

ለጥያቄ ተፈልጎ በፈቃደኝነት አቴንስ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አምርቶ የነበረው ተዋናዩ ከዚያ በኋላ በትናትናው እለት በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠበቃው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኘው ተዋናዩ በቅርቡም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ኢካቲሜሪኒ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

ተዋናዩ ከብሄራዊ ቲያትር ዳይሬክተርነቱ ስልጣን ለቅቄያለሁ ያለው ባለፈው ወር ሲሆን ይህም በስራ ቦታው ላይ "አሉባልታዎች እየተነዙ ፤ እውነታ የሌላቸው መረጃዎች እየወጡ ስለሆነ ስራዬን ሊያሰራኝ አልቻለም" የሚል ምክንያት አቅርቦ ነበር።

ከሰሞኑ ስመ ጥር ግሪካውያን ከወሲባዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ስማቸው እየተጠራ ሲሆን የቀድሞ የግሪክ ኦሎምፒክ አሸናፊ ሶፊያ ባካቶሩ የሄሊኒክ ሴይሊንግ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥቃት አድርሶብኛል ስትል አጋልጣለች።

አትሌቷ የግለሰቡን ማንነት ባትጠቅስም ሁኔታው በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል፤ በርካቶችም ጉዳዩን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ወስደውታል።

በባለፉት አመታት በአለም ላይ ወሲባዊ ጥቃትን አስመልክቶ በማህበራዊ ድረ ገፆች ሚቱ የሚለው ዘመቻ የተቀጣጠለ ሲሆን በግሪክም ይህ ሁኔታ መነሻ ሆኗል ተብሏል።

2px presentational grey line