በዱባይ የሴቶች መብቶች የትኞቹ ናቸው?

በቅርቡ ዓለምን ካስደነገጡ ጉዳዮች በአንዱ እንጀምር- የልዕልት ላቲፋ ጉዳይ። ልዕልቷ የዱባዩ ገዥ ልጅ ናት፡፡
ልዕልቷ በድብቅ ተቀርጾ ቢቢሲ እጅ በገቡት ተንቀሳቃሽ ምስሎች በጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ለመሸሽ ከሞከረችበት ጊዜ አንስቶ አባቷን በከተማው እንዳገቷትና አባቷን ከመክሰስ ባለፈ ሕይወቴም አደጋ ላይ ነው ትላለች።
ስለ ጉዳዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን (UAE) እጠይቃለሁ ብሏል፡፡ ልዕልቷ ለመሰደድ የተነሳች ብቸኛዋ የቤተሰቡ አባል አይደለችም፡፡
ልዕልት ሀያ ቢንት ሁሴን 45 ዓመቷ ሲሆን የልዕልት ላቲፋ አባት ሚስት ናት። በጎርጎሮሳዊያኑ ሰኔ 2019 ወደ ጀርመን ተሰዳ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቃለች፡፡ የላቲፋ እህት ሻምሳም ለማምለጥ ሞክራለች፡፡
በባህረ ሰላጤው ባለስልጣኖች በሆኑት በአንዱ ላይ የሚቀርቡት የጭቆና፣ የማጎሳቆል እና የቁጥጥር ውንጀላዎች የሚረብሹ ናቸው፡፡
ሴቶች በሕይወታቸው ውስጥ መብቶቻቸው እና ዕድሎቻቸው በወንዶች እንዴት ይወሰናል? የሚለውን እንመልከት፦
በዱባይ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ስለሚኖሩሴቶች ምን ማለት ይችላል?
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሴቶች ማሽከርከር፣ መምረጥ፣ መሥራት፣ ንብረት ማፍራት እና መውረስ ይፈቀድላቸዋል፡፡
ከዓለም ኢንፎርሜሽን ፎረም የተገኘው ሪፖርት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ክልል በጾታ እኩልነት ሁለተኛ ደረጃን እንደያዘች ያስቀምጣል። ሆኖም ዐውዱን መረዳት አስፈላጊ ነው።
በዓለም አቀፉ የሥርዓተ ፆታ (Gender Gap) ዘገባ መሠረት አካባቢው ከሌሎቹ አንጻር በጣም ዝቅተኛ ውጤት ነበረው። ከእስራኤል በስተቀር አንዳቸውም እስከ 100 ባለው ደረጃ ውስጥ ውስጥ አልገቡም፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከዓለም 153 ሀገራት 153ኛ ደረጃን ይዛለች።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የፀረ መድልዎ ሕግ ቢኖራትም፤ ፆታን መሠረት ያደረጉ አድሎዎች በሕጉ ፍቺ ውስጥ አልተካተቱም፡፡
ሴቶች መብቶች ቢኖራቸውም፣ በግላዊ ሕጉ መሠረት ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በወንድ “ሞግዚት” መፅደቅ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ይህም ማለት ሴቶች ብዙውን ጊዜ ፈቃድ እንዲያገኙ የሚፈቅደው የትዳር ጓደኛ ወይም ሌላ ወንድ ዘመድ ነው፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሕጎች እንደ ጎረቤት ሳዑዲ አረቢያ ጥብቅ ወይም ሰፋ ያሉ ባይሆኑም በሴቶች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ሴቶች መብቶች በሚኖራቸው ወቅትም በፍርድ ቤት የመከላከሉ ጉዳይ በተግባር ሲታይ ከባድ ነው፡፡
ጋብቻና ፍቺ
ፈተና ከገጠመው የሴቶች የግል ሕይወት አንዱ ጋብቻ ነው። አንድ ሴት ለማግባት የወንድ ሞግዚት ፈቃድ ያስፈልጋታል፡፡ ሌላው ደግሞ የልጆችን ጥበቃ እና ውርስን ያካትታል።
በሕግ ያልተስተካከሉ ግን በተግባር የሚከናወኑ ኦፊሴላዊ ያልሆኑ የአሳዳጊነት ዓይነቶችም አሉ ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዋች ተመራማሪ የሆኑት ሂባ ዛያዲን ለቢቢሲ ዜና ተናግረዋል፡፡
"በእርግጥ በሕጉ በማይገኙባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎችም ሴቶች ሥራ ለማግኘት በሚያመለክቱበት ጊዜ ወይም ቤት ለመከራየት ሲፈልጉ ከአሳዳጊዎቻቸው ፈቃድ ይጠይቃሉ። ይህ ግን በሕጉ ውስጥ የለም። ጋብቻን እና ፍቺን በተመለከተ ግን በሕጎቹ ውስጥ በጣም ግልጽ ተቀምጧል” ብለዋል፡፡
ፍቺም ሌላው ለሴቶች ከባድ ጉዳይ ነው፡፡ ወንዶች በተናጥል መፍታት ቢችሉም፣ ሴቶች መፋታት ከፈለጉ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በቤት ውስጥ የሚፈጸሙጥቃቶች
ሴቶች ላይ ያለው መድልዎ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችም ያጠቃልላል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቢያንስ በመሬት ላይ አንዳንድ አዎንታዊ የሕግ ለውጦች ተደርገዋል፡፡
ለምሳሌ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሕግ በግልፅ ወንዶች ሚስቶቻቸው ላይ ጠበኛ እንዲሆኑ ይፈቅድ ነበር። ነገር ግን በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 ላይ ተሰርዟል፡፡
የሴቶች ለባሎቻቸው “ታዛዥ” እንዲሆኑ የሚጠይቀው ሕግ ደግሞ በ2019 ተሽሯል፡፡ ባለፈው መጋቢት ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስችል አዲስ ሕግም ተፈጻሚ ሆኗል፡፡ ተጨማሪ የሕግ ማሻሻያዎች ባለፈው ዓመት መጨረሻም ነበሩ፡፡
ሆኖም ግን ሕጎቹ ብዙም ርቀት አይሄዱም የሚሉ ደምጾች ተሰምተዋል፡፡ አዲሱ ሕግ የቤት ውስጥ ጥቃትን የሚወስነው በዳኛ የግል አስተያየት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በተግባር የጥቃት ሰለባዎች ጥበቃ አሁንም ደካማ ነው ማለት ይቻላል፡፡
“በግዛቲቱ በጾታ እኩልነት ላይ ጥላቻን የሚያሳዩ ሕጎች አሉ። በሕገ መንግስቱ ላይ የፃፋቸውን እጅግ አስጸያፊ ነገሮችን በማስወገድ ይመስላል” ሲሉ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል የባህረ ሰላጤው ተመራማሪ ዴቪን ኬኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
አምነስቲ በጎርጎሮሳዊያኑ 2014 በአገሪቱ አድሎአዊ ሕጎችን የሚተች ዘገባን ካወጣበት ወቅት ጀምሮ ምርምራ ለማድረግ ወደ አረብ ኤምሬትስ መግባት አልቻለም፡፡
“ስለሆነም በስርዓተ ፆታ ጥያቄዎች ላይ ያላቸው አመለካከት ምን እንደሆነ ለማየት በሚወጡት ሕጎች ላይ የመመስረት አዝማሚያ ነበረን። ለውጦች ተደርገውም በእነዚያ ሕጎች ውስጥ ብዙ ኢ-ፍትሀዊነት አለ፡፡ ይህ በማኅበራዊ ወይም በመንግሥት አመለካከቶች ላይ ምንም ዓይነት ጥልቅ ለውጦችን አያመለክትም” ብለዋል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ የሚኖር ወይም የሚጎበኝ ማንኛውም ሰው ለሕጎቹ ተገዢ ነው። ቱሪስቶች በዚህ ውስጥ ይካተታሉ፡፡
በዱባይ በእረፍት ላይ ሳሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችም አሉ። ለምሳሌም በጎርጎሮሳዊያኑ 2017 አንዲት እንግሊዛዊ ሴት ካላገባችው ወንድ ጋር በስምምነት ወሲብ ፈጽማ በመያዟ የአንድ ዓመት እስራት ተፈረዶባታል፡፡
የማስፈራሪያ መልዕክቶችን ስለላከላት ለባለስልጣናት ሪፖርት ስታደርግ ነበረ ሁለቱ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸማቸውን ያወቁት፡፡ በእውነቱ እነዚህ ሕጎች በእኩልነት የሚተገበሩ መሆን አለመሆኑ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡
የመደብ ክፍፍል
ቀደም ሲል ይፋዊ ያልሆነውን መደብ ሕግ ተደርጎ ተቀምል።
በመደቡ አናት ላይ የሚገኙት ሀብታም ሴቶች ሲሆኑ የኤሚሬትስ ሴቶች ሁለተኛ፣ ቀጥሎ ደግሞ ስደተኛ የቤት ሠራተኞች ይመጣሉ፡፡
“የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይህንን የመደብ ክፍፍል ወደ ተቋማዊነት እየቀየረች ይመስላል፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የሕግ ማሻሻያ ሲተዋወቅ የመንግሥት የዜና ወኪል የሆነውን ዋምን ጨምሮ በሌሎችም ዓላማው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ አገሪቱን የበለጠ ለማሳደግ እና ጥሩ የኢንቨስትመንት አካባቢን በመፍጠር የውጭ ዜጎችን ለመማረክ ነው በሚል በይፋ ዘግበዋል” ሲሉ ኬኒ ገልጸዋል።
“ውርስ እና ፍቺ የሚመለከቱ ህጎች ላይ የተደረጉት ለውጦች የሚመለከታቸው ለኤሚሬትስ ሴቶች ሳይሆን የውጭ አገር ሠራተኞችን (expatriates) የሚመለከት ነው ተብሎ በብሔራዊ ጋዜጣ በግልፅ ተዘግቧል” ይላሉ።
እንደ ዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት (ILO) መረጃ ከሆነ በጎርጎሮሳዊያኑ 2017 አነስተኛ ደመወዝ ያላቸው ስደተኛ ሠራተኞች “እጅግ በጣም የዝቅተኛ ተጠቃሚ መደብ ላይ ቢሆኑም” ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር 80% ያህሉን ይሸፍናሉ ይላሉ ኬኒ፡፡
በተለይም ከደቡባዊ እና ደቡብ ምስራቅ እስያ የመጡ የቤት ሠራተኛ ሴት ስደተኞች ከባድ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡ እንደ ኬኒ ገለጻ በማይታመን ሁኔታ ውስን መብቶች አላቸው። የወንጀል ሕጉን አንቀጽን በመጥቀስ ‘በመስማማት ክብርን መጣስ’ ሊያስከሰስ ይችላል ይላሉ፡፡
በተግባር ግን የስምምነት ወሲብ ላይ ለማነጣጠር ጥቅም ላይ ይውላል ይላሉ፡፡ “በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በእርግዝና ምክንያት ወደ ሆስፒታል የሚያቀኑ ሴት ስደተኛ የጉልበት ሠራተኞች ለእርግዝናው ኃላፊነት የሚወስድ አባት ሲያጡ በዚህ ሕግ መሠረት ክስ ይመሠረትባቸዋል” ብለዋል፡፡
ከጋብቻ ውጭ ያረገዙ ሴቶች እስከ አንድ ዓመት እስራት ይጠብቃቸዋል። ስደተኛ ሠራተኞች ቅጣቱ የሚፈጸምባቸው አገሪቱን ከመልቀቃቸው በፊት፡፡
ባለፈው ዓመት ጋርዲያን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደገለጸው፤ በአገሪቱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ሴቶች ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆች አሏቸው፡፡
የተደፈሩ ተጎጂዎችም ከጋብቻ ውጭ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን በሚመለከቱ ሕጎች ጉዳያቸው ታይቶ ክስ ይመሠረትባቸዋል፡፡
በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 የቢቢሲ አረብኛ ምርመራ እንዳመለከተው የመድፈር ተጎጂዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በየአመቱ በዚህ ሕግ ለእስር ተዳርገዋል።
ለዚህ ደግሞ የቤት ሠራተኞች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡












