"ለምን ስሜን ለ20 ዓመታት ደበቅኩ?"

የአፒያህ-ዳንጓህ ምስል

የፎቶው ባለመብት, MiriYame አፒያህ-ዳንጓህ

የምስሉ መግለጫ, አፒያህ-ዳንጓህ ስሟን ለማስመለስ 20 ዓመት ፈጅቶባታል

ለእኛ ስም ማለት ቁልፍ ነገር ነው። ስማችን ከታወቀ አዲስ ያልተነገረ ታሪክ ሊያጋልጥ ይችላል። ታዲያ ሌሎቹን ለማስደሰት ሲባል ስንቀይረው የሚያደርሰው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?

'የእኔነቴን ትልቅ ነገር ደብቄያለሁ'

"በ1980ዎቹ አጋማሽ እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ምስራቅ ለንደን ውስጥ ማደግ አሁን እንዳለው አልነበረም" ትላለች ሚሪያም አፒያህ-ዳንቋህ። "አንደኛ ደረጃ ስንማር እኔ ከአምስት ጥቁሮች መካከል አንዷ ስሆን በተጨማሪ አንዲት ህንዳዊት ነበረች። ቀሪዎቹ ግን ሁሉም ነጮች ነበሩ" በማለት ታስታውሳለች።

"አንዱ የቆየው ትዝታዬ መዋዕለ ሕጻናት እያለሁ እናቴ 'ትዊ' ብላ የጠራችኝ ነው [ጋና ውስጥ የሚነገር ቋንቋ ነው]። ያኔ ሦስት ወይም አራት ዓመት ቢሆነኝ ነው። እናም "ይህንን ቋንቋ እዚህ አንናገርም" ነበር ያልኳት።

"በእርግጠኝነት በአፍሪካዊነቴ እንዳፍር እና በዚያ እድሜዬ እንደዚያ መናገር ማለት የሆነ አካል እኔነቴ ትክክል አለመሆኑን ይነግረኛል የሚል እሳቤ የነበረኝ ይመስለኛል"

"አስታውሳለሁ፣ ከጥቁር አፍሪካዊ ጋር በመጣመሬ እና የተለየ የጸጉር አሰራር ስለነበረኝ ብቻ ከተማሪ እስከ ተማሪ መዘባበቻቸው ነበርኩ።

የሚሪያም አፒያህ-ዳንቋህ ምስል

የፎቶው ባለመብት, ሚሪያም አፒያህ-ዳንቋህ

የምስሉ መግለጫ, ሚሪያም በ 'ብላክ ላይቭስ ማተር' ወቅት በኢንስታግራም ድምጽ ለመሆን ተነሳስታ ነበር

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ስትጀምር ሚሪያም ዳንቋህ የሚለውን ስም በትምህርት ቤት ውስጥም ሆነ የመማሪያ ደብተሯ ላይ መጻፏን አቆመች። ይህ የሆነው ደግሞ አስተማሪዎቿ ስሙን መጠቀም እንደሌለባት ትዕዛዝ በመስጠታቸው ነበር። ከዚያም ቀደም ብላ ያገኘቻቸው የምስክር ወረቀቶች ሁሉ ላይ ሳይቀር እየለቃቀመች ስሟን ማጽዳት ዋነኛ ሥራዋ ሆነ።

"ሁሉም ብራውን፣ ስሚዝ፣ ዋይት ወይም ጆንስ እየተባለ ሲጠራ የእኔው ስም ግን ረጅም እና የተለየ ሆነ። እናም ያ አፍሪካዊነቴን ስለሚያስባንን የትኛውም ሰነድ ላይ ስሜ እንደይገኝ ማድረግን ቀዳሚ ሥራዬ አደረግኩ።

"ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ከዚያ ሥራ ጀመርኩ። ዳንቋህ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል፤ ማንም አያውቀውም ነበር። ምክንያቱም ከማንኛውም ሕጋዊ ሰነድ ላይ ስላስወገድኩት ማንም አላወቀውም ነበር።"

ባለፈው ሰኔ ዓለም አቀፉ የብላክ ላይቭስ ማተር አመጽ ሲቀጣጠል ከ20 ዓመታት በኋላ ሚሪያም ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ስሟን በኢንስታግራም ጻፈች።

"የጆርጅ ፍሎይድ መገደል እና ቀጥሎ የመጣው ተቃውሞ ለእኔ ትልቅ የማንቂያ ደወል ነበር። ትልቁን አኔነቴን ደብቄው መቆየቴ ተገለጸልኝ። ይህ ደግሞ የእራሴን ማንነት እና ጥቁርነቴን የሚያካትት ነው" ትላለች የ34 ዓመቷ አካውንታት።

"የእርሱ ሞት የመጨረሻ ደወል እና ብዙዎቹን ወደፊት ያመጣ፣ ምናልባትም ለብዙዎቻችን ወደ ትክክለኛ ማንነታችን [ጥቁር ማንነት] የመለሰ ነው። ጥቁር በመሆናችን ራሳችንን ጨቁነን ነበር፤ ሰላም ማስፈን መርጠን ጥቁር በመሆን ተቀባይነት የማያስገኙ ብለን የደበቅናቸው ነገሮች ነበሩ።

"የመጣልኝ ሃሳብ ለዓመታት የኖርኩት ኑሮ የውሸት እንደነበር ነው፤ ንዑስ ማንነቴን መኖር ስለማይገባኝ እንደ ጥቁር ሴት ሙሉ ሆኜ የምኖርበትን ሁናቴ መፈተሽ ግድ ይለኛል።"

ሙሉ ስሟን የሚገልጽ ጽሑፍ ካጋራች በኋላ ሚሪያም ነጻነት ተሰምቶኛል ትላለች። ይህ ጽሁፏም እስከዛሬ ካጋራቻቸው ጽሁፎች ሁሉ ላቅ ያለ ተወዳጅነትን ያተረፈ እና "በርቺ" አይነት በርካታ ኮመንቶችንም አስተናግዷል።

"ስሜት የሚነካ ነበር፤ እናም አልቅሻለሁ" ትላለች። "ልክ ሰዎች እና ማህበረሰቡ እኔን በእኔነቴ እንዲገልጸኝ ለማድረግ ራሴን ይቅር እንደማለት ያክል ነበር።

"አፒያህ ማለት ልዑል ማለት ሲሆን ዳንቋህ ደግሞ ዘላለማዊ ሕይወት ማለት ነው። ታዲያ ይህ ለምን ይደበቃል? ይህ ስሜ ነው፤ እኔ ማለት እንደዚህ ነኝ።"

'የማንነት ቀውስ ነበረብኝ'

የራኪሻና ካንዋል ኢጃዝ ምስል

የፎቶው ባለመብት, ራኪሻና ካንዋል ኢጃዝ

የምስሉ መግለጫ, ራኪሻና ካንዋል ኢጃዝ ስሟን በመደበቅ ሮክሲ ብለው እንዲጠሯት አድርጋ እንደነበር ተናግራለች

ራኪሻና ካንዋል ኢጃዝ ተወልዳ ያደገችው በእንግሊዝ በርሚንግሃም ሲሆን ከፓኪስታን ተሰደው ከመጡ ቤተሰቦች የተገኘች ነች።

እንደሚሪያም ሁሉ ራኪሻና ከስሟ ጋር ትግል የጀመረችው ከትምህርት ቤት ነው። ሌሎች ሲጠሩትም ሆነ ሲያነቡት ቀላል ይሆንላቸዋል ባለችው ስም ቀይራ ተመዘገበች። ምክንያቱም አንዳንድ አስተማሪዎች ራኪሻና የሚለውን ስሟን ፊደላት በናጉደል ራክሻና ወይም ራክሳና ይሉታል።

"አይ! መጻፍ ያለበት እንደዚህ ነው ስል በተወሰነ ደረጃ ቁጣ ይሆንባቸዋል፤ ነገር ግን የተወሰነ ነገር ካልኩ ድርቅና ተደርጎ ይቆጠራል" ትላለች።

ይመስለኛል ያ ስሜን እንድጠላው አድርጎኛል፤ እናም ሳድግ ስሜን እቀይራለሁ እያልኩ ለቤተሰቦቸ እቀልድላቸው ነበር።"

የ27 ዓመቷ ወጣት በአባቷም በማህበረሰቡም ስም ቢወጣላትም ችግሮች ገጥመዋታል።

"ስሜ የተለመደ አይደለም፤ ምክንያቱም መነሻው ፐርሽያ ስለሆነ- ፋርሲ እና ኡዱ ይባላል። እናም ፓኪስታኖች እና ሌሎች ሙስሊሞች ሳይቀሩ ስምሽ ከየት የመጣ ነው ብለው ይጠይቁኛል።

"እናም ለተወሰነ ጊዜ ከየት እንደሆንኩ ስለማላውቅ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብቼ ነበር፤ የማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ለመጥራት ስለሚቸገሩ ለእኔ ከባድ ነበር።"

ራኪሻና እንደምትለው በእዚህ ምክንያት ያዳበረችው የዝቅተኝነት ስሜት ዩኒቨርስቲ ስትማር ከዚያም ሥራ እስክትጀምር ድረስ አብሯት ቆይቷል።

"ስሜን አልጠላሁትም፣ ግን ደግሞ ማካካስ ነበረብኝ" የምትለው ራኪሻና "ጓደኞቼን 'ሮክሲ ብላችሁ ጥሩኝ' እላቸዋለሁ። እናም ከተወሰኑ ሥራዎች በኋላ ሮክሲ ወይም ሮክሳኔ በሚል ታወቅኩ፤ ማንም ግን እውነተኛ ስሜን አያውቀውም።

"ወደኋላ ስመለከት፣ ሳያውቁኝ መኖራቸው ምን ያክል የሚያናድድ መሆኑን አስባለሁ።"

ራኪሻና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፊት ስሟን ቀይራ እንደነበር ማሳወቅ ጀምራለች። ከዚያም ባል ስታገባ የባሏን ስም ደርባ መያዝ እንዳለባት ወስና በዚያው ቀጥላለች።

"አባቴ ያወጣልኝን ስም ማጣት አልፈልግም። ካንዋል ማለት የውሃ ላይ አበባ ወይም ጣፋጭ ፍሬ ማለት ነው። ሁልጊዜ እንደዚያ ነው የሚጠራኝ።

"ስሜን ትቼ በባሌ ስም ብቻ መወሰን አልፈለግኩም። ምክንያቱም ከባሌ በፊት የነበረው እኔነቴ አሁን ላለኝ ማንነቴ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ወደፊትም ይሆናል። እናም ያንን የህይወቴን ክፍል ማስወገድ አልችልም። ስም ብዙ ኃይል ይሸከማል።"

የራኪሻና አባት ባለፈው ዓመት አርፈዋል። እናም እራሷ ቤተሰብ በመመስረቷ ሰዎች ትክክለኛ ስሟን እንድትይዝ እየጎተጎቷት ነው።

"አባቴ በስሜ ሁሌ እነደኮራ ነበር፤ ነገር ግን ወጣት እስክሆን ድረስ ስሙ ለምን እንደተሰጠኝ አልገባንም ነበር" ብላለች የሁለት ልጆች እናቷ ራኪሻና።

"አሁን በእሱ ምክንያት በእኔነቴ ኮርቼው የማላውቀው ኩራት እየተሰማኝ ነው። ሁሉም ለእኔ ያደረገው ነገር ሁሉ ያኮራኛል።"

"አሁን ተመልሼ ወደኋላ ስመለከት፣ ሌሎቹን ለማስደሰት ሲባል የራሴን ስም ለ20 ዓመታት ማሳሳቴ ምን ያክል እብደት እንደሆነ ነው የገባኝ" ትላለች።

"ለሰዎች ሲባል ማንነታቸውን መቀየር እንደሌለባቸው ነው ለሰዎች የምናገረው። ለሌሎች ሰዎች ድክመት ሲባል የእኔን ስም ማሳሳቴን አቁሜያለሁ።

"ዳዕነሪስ ታርጋሪየን [ጌም ኦፍ ትሮንስ] የሚለውን መጥራት ከቻልን ብዙ ልንጠራቸው የምንችላቸው ስሞች አሉ። ዋናው መሞከሩ ነው"

'ስምሙ ለመሆን እፈልግ ነበር'

የግሪጎሪጂ ሪቸርስ ምስል

የፎቶው ባለመብት, ግሪጎሪጂ ሪቸርስ

የምስሉ መግለጫ, ግሪጎሪጂ ሪቸርስ ለሥራው ያመቸው እንደሁ በሚል ስም መቀየሩን ያስታውሳል

ገሪጎሪጂ ሪቸርስ የተወለደው ጀርመን ቢሆንም የቼክ ዜግነት ያላት እናቱ ያወጡለት ስም ግን የሩሲያ ነው። ስምሙ ለመሆን ሲባል የ15 ዓመት ታዳጊ እያለ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለአዳሪ ትምህርት ቤት ሲላክ ስም መቀየሩን ይናገራል።

"ስሜ ግሪ-ጎ-ሪጅ ተብሎ ነው የሚነበበው፤ በእንግሊዝኛ ሲሆን ግን ክራይግ-ሪጅ ይሆናል። ስለዚህ እንደ አንድ ደኅንነቱ እንደሚያሰጋው ታዳጊ ስሜን ቀይሬ ስምሙ መሆንን መረጥኩ ይላል የ33 ዓመቱ ጎልማሳ።

"በትምህርት ቤቱ ውስጥ በእኔ የሚያላግጡ እና የሚዝናኑ ብዙ ተማሪዎች ነበሩ፤ አንዳቸውም ስሜን በትክክል አይጠሩትም። እናም ሰላማዊ ነው ብዬ አላስብም ነበር።

"ከዚያ ግሬግ ተባልኩ ከዚያ ደግሞ ግሪጎሪ"

ግሪጎሪጅ በሕጻንነቱ የፊልም ተዋንያን ለመሆን ያልም ነበር፤ ለእዚህ ኢንዱስትሪ ደግሞ ለአፍ የሚቀል ስም ያስፈልጋል ብሎ በማመኑ አንደኛው ስሙን የመቀየሪያው ምከንያት ሆኗል።

"ለእኔ ያን ያክል አስፈሪ ነገር አልነበረም፣ እንዲሁ ለሰዎች ነገሮችን ቀላል ላድርግላቸው ከሚል እሳቤ የተነሳ ነው።"

ወጣት ሲሆን ስሙን በመቀየሩ ተጸጽቷል፤ ነገር ግን ገና ታዳጊ እያለ ደስ ይሰኝ ነበር።

"ነጭ ነኝ፣ እከበራለሁ፣ አውሮፓ ውስጥ ነው የምኖረው- እና እነዚህን ሁኔታዎች ሚዛን ላይ አስቀምጠናቸው የእኔን ስም አስቸጋሪነት ስንመዝነው ብዙም ውሃ የሚያነሳ ጉዳይ አይደለም።

"ሁላችንም ቅድሚያ የምንሰጣቸው ጉዳዮች አሉ፤ በዚያ ወቅት ለእኔ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ስሜን የሚመች አድርጎ ከቡድኑ ጋር ስምሙ መሆን ነበር፤ ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው።

"ለእኔ እውነት ለመናገር ስምን መቀየር በ15 እና 16 ዓመት እድሜዬ ወቅት ትልቅ ጉዳይ እንደነበር ተመልሶ ማሰብ በራሱ አስቂኝ ጉዳይ ነው።"