ኮሮናቫይረስ፡ 33 ሚሊዮን ፓውንድ ያሰባሰቡት የ100 አመቱ ሽማግሌ በኮቪድ-19 ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በእንግሊዝ ለጤና ባለሙያዎች ያላቸውን ክብር ለመቸር 33 ሚሊዮን ፓውንድ በማሰባሰብ ከፍተኛ ስም ያተረፉት ካፕቴን ቶም ሙር በመቶ አመታቸው በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አልፏል።
33 ሚሊዮን ፓውንድ ለአገሪቱ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ወይም ኤንኤችኤስ ማሰባሰብ የቻሉት የ100 አመቱ የዕድሜ ባለፀጋ በባለፈው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ከመተንፈሻ እክል ጋር በተያያዘ ቤድፎርድ ወደተባለ ሆስፒታል ተወስደው ነበር።
ልጃቸው፣ ሃና ኢንግራም ሙር በባለፉት ሳምንታት በሳንባ ምች ህመም ሲሰቃዩ እንደነበርና በዚህ ሳምንት በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ ተናግራለች።
ግለሰቡ የ2ኛው የዓለም ጦርነት ተዋጊ ሲሆኑ ከቤታቸው ጓሮ በሚገኘው ሜዳ 100 ዙር በመሮጥም ነው የእርዳታ ገንዘብ ያሰባሰቡት። ይህንንም ያደረጉት ከመቶኛ አመት ልደታቸው በፊት ነው።
ልጆቻቸው ሃና ኢንግራም ሙርና ሉሲ ቲየክሴራ እንዳሉት "ውድ አባታችን ካፕቴን ሰር ቶም ሙር መሞታቸውን በታላቅ ሃዘን ነው የምንናገረው" ብለዋል።
በመጨረሻው ሰዓትም ከአባታቸው ጎን በመሆናቸው ትልቅ ክብር እንደነበር ገልፀዋል።
"ለሰዓታት ያልህ ስለ ልጅነታችን፣ ስለ ውዷ እናታችን ስናወራ ነበር። ረዥም ሰዓት ሳቅን፣ አለቀስን። አባታችን በባለፈው አመት አስቦትና አልሞት የማያውቀው ነገር ተሳክቶለታል። "ብለዋል
አክለውም "ምንም እንኳን ለአጭር ወቅት ቢሆን በብዙዎች ልቦና ዘንድ የማይረሳ ነገርን ጥሏል። ለኛ አስደናቂ አባት፣ አያት ነው፤ ሁልጊዜም ቢሆን በልባችን ይኖራል" በማለት ኃዘናቸውን አጋርተዋል።
የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ለአባታቸው ያደረጉላቸውን እንክብካቤ አድንቀዋል።












