ፍትህ ለዓለማችን 'ታዋቂው ዘፈን' አቀናባሪ

ደቡብ አፍሪካዊው ሶሎሞን ሊንዳ በፈረንጆቹ 1962 ነው የሞተው

የፎቶው ባለመብት, SA POST OFFICE

በዝምባቡዌያውያን ዘንድ እንደ ሙዚቃ አባት የሚቆጠረው ሙንያ ቻኔስታ አሜሪካዊያን አንድ የሙዚቃ ሥራን 'የኔ ነው'፤ 'የኔ ነው' ሲባባሉ ሲመለከት አንዳች ነገር ወረረው።

ሙዚቃው 'ዘ ላየን ስሊፕስ ቱናይት' ይሰኛል። ስለአንበሳ ከተሠሩ ሙዚቃዎች በዓለም ተወዳጁ ነው ይባልለታል።

የሙዚቃው የመጀመሪያ መጠሪያ ምቡቤ ነው።

የዚህ ሙዚቃ አቀናባሪ ደቡብ አፍሪካዊው ሶሎሞን ሊንዳ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በፈረንጆቹ 1962 ነው የሞተው።

በዚህ ጥዑም ዜማ ምክንያት አሜሪካውያን አርቲስቶች ብዙ ሲባጠቁ ሶሎሞን ግን በኩላሊት ሕመም ምክንያት በሆስፒታል አልጋው ላይ ሲሰቃይ ነበር።

በፈረንጆቹ 2019 ኔትፍሊክስ በተሰኘው የበይነ መረብ ፊልም ማከራያ ገፅ ላይ የተለቀቀ አንድ ዘጋቢ ፊልም የዚህን ሙዚቃ አመጣጥ ይቃኛል።

በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ ደቡብ አፍሪካዊው ፀሐፊ ራያን ማላን ታዋቂው ሙዚቃ የሶሎሞን ሥራ እንደሆነ አብጠርጥሮ ያስረዳል።

ሶሎሞን ይህን ሙዚቃ ከዙሉ ብሔረሰብ ሕብረ ዘማሪዎች [አካፔላ] ጋር በመሆን ነው የሠራው።

ይህ የሙዚቃ ዲዝኒ የተባለው የፊልም አምራች በ1994 የለቀቀው ዝነኛ የካርቱን ፊልም 'ዘ ላየን ኪንግ' ማጀቢያ ነው።

ነገር ግን የሶሎሞን ቤተሰቦች አሁንም በድህነት እየማቀቁ ነው።

ቻኔስታ ይህን ዘጋቢ ፊልም ከተመለከተ በኋላ ልቡ በጣም እንደተነካ ይናገራል። አፉን በእጁ ሸፍኖ ግን አልተቀመጠም። ስለ ሶሎሞን ማጥናት ጀመረ።

ሶሎሞን በፈረንጆቹ 1939 ጆሃንስበርግ በሚገኘው ኢቭኒንግ በርድስ የሙዚቃ ስቱዲዮ ይሠራ ነበር። በዚህ ወቅት ነው ይህን ሙዚቃ ከሕብረ ዘማሪዎቹ ጋር በመሆነ የሠራው።

"ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው ሥራ አሁን ላይ የባለቤትነት መብት የለውም። የሕዝብ ሥራ ነው ማለት ነው። ያኔ ነው ሁሉ ነገር የሚጀምረው።"

የሙዚቃውን ቃና እያቃና ይህን ዘመን ተሻጋሪ ሥራ የሠራው ሶሎሞን በወቅቱ ለሙዚቃው 10 ሺሊንግ ነበር የተከፈለው።

ነገር ግን ይህ ሥራ በ1940ዎቹ ታዋቂነቱ እየጨመረ መጣ።

ይህ ሙዚቃ ባህር ተሻግሮ አሜሪካ ገባ። በወቅቱ በሐገረሰብ ሙዘቃ አሜሪካዊያንን ሲያስጨፍሩ የነበሩት ዘ ዊቨርስ ህን ሙዚቃ ተንተርሰው የራሳቸውን ሥራ ለሕዝብ አቀረቡ።

የነሱ ሥራ መጠሪያው ዊሞዌህ ነበር። በሶሎሞን ሥራ ላይ ሕብረ ዘማሪዎቹ 'ዊዩምቡቤ' እያለ ሲዘፍኑ የሰሙት አሜሪካዊያኑ ሙዚቀኞች 'ዊሞዌህ' መስሏቸው በዚህ ሰየሙት።

'ዊዩምቡቤ ማለት በዙሉ ቋንቋ 'አንተ አንበሳ ነህ' ማለት ነው።

የሶሎሞንን ሕይወት ያጠናው ቻኔስታ ሙዚቃው የተሰራው በደቡብ አፍሪካ በልጅነት ዘመን እረኞች ከአንበሳ ጋር ያላቸውን ትንቅንቅ ለማሳየት ነው ይላል።

የሐገረሰብ ሙዚቀኞቹ ይህን ሙዚቃ ለአሜሪካዊያን ጆሮ እንዲስማማ አድርገው የሠሩት በ1950ዎቹ ነው።

በ1960ዎቹ አሜሪካዊው የሙዚቃ ግጥም ገጣሚ ጆርጅ ዴቪድ [In the jungle, the mighty jungle, the lion sleeps tonight] የሚል እንግሊዝኛ ግጥም አክሎበት ዘ ቶክንስ ለተሰኘው ባንድ ሰጠው።

ይህ 'ዘ ላየን ስሊፕስ ቱናይት' የተሰኘው ሥራ ነው አሁን የዚህ ሙዚቃ የመብት ባለቤት።

ቻኔስታ ምቡቤ የተሰኘውን የመጀመሪያውን ሙዚቃ እንደ አዲስ ሠርቶ ለሕዝብ ማቅረብ ይፈልጋል።

"ከሶዌቶ ጎስፕል ኳየር ጋር የዚህን ሙዚቃ ክብር ለመመለስ እየሠራሁ ነበር" ይላል ለሶኒ የሚሠራው የሙዚቃ አቀናባሪው ቻኔስታ።

ነገር ግን ይህ አልሳካ ሲለው ዘ ማሆቴላ ክዊንስ እየተባሉ ከሚጠሩት ደቡብ አፍሪካዊያኑ ሴት አቀንቃኞች ጋር ለመሥራት አቅዷል።

ከእነዚህ ሙዚቀኞች ባለፈው ከሁለት 'ዲጄዎች' ጋር ተባብሮ ዘመናዊ ቅመም ሊያስገባበት አቅዷል።

ቻኔስታ ከዚህ ሙዚቃ ገቢ 45 በመቶው ለሶሎሞን ቤተሰቦች የሚሆን ነው ይላል።

ምንም እንኳ አሜሪካዊያኑ ሙዚቀኞች እንደሚያገኙት ረብጣ ዶላር ባይሆንም ምናልባትም ሶሎሞን ሊንዳ በቻኔስታ ሥራ ፍትህ ያገኘ ይሆናል።