የዝሆን ልጅ [ኤልሞሌ] ከሞት የታደገው ታይላንዳዊ

የአደጋ ጊዜ ሠራተኛው ለኤልሞሌው የመጀመሪያ እርዳታ ሲሰጠው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአንድ ምሽት ታይላንድ ውስጥ የዝሆን መንጋ መንገድ እያቋረጠ ነበር። ከመንጋው መካከል ግን አንዱ ኤልሞሌ፣ የዝሆን ልጅ፣ እየከነፈ ሲመጣ በነበረ የሞተር ብስክሌት ተገጭቶ ተዘረረ። በዚህ ወቅት በመደበኛ ሥራው ላይ ያልነበረ ታይላንዳዊ የአደጋ ሠራተኛ ለኤልሞሌው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጠት ጀመረ።

ይህንን የግለሰቡን ተግባር በተንቀሳቃሽ ምስል ያስቀሩ ሰዎች ዜናውን ለዓለም አዳረሱት። ኤልሞሌውንም በተሰጠው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መትረፍ የቻለ፣ ግለሰቡም ለዝሆን እርዳታ በመስጥ ወሬያቸው ናኘ።

የሕክምና እርዳታው የኤልሞሌው ትንፋሽ እንዲመለስ ደረቱን በአግባቡ ጫንጫን ማለትን ያካተተ ነበር ተብሏል።

ማና ስሪቫቴ ይባላል ታይላንዳዊው የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ። እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ ይህ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ በሥራ ሕይወቱ በርካታ የሕይወት ማትረፍ ሥራዎችን ቢያከውንም የዝሆን ሕይወትን ከሞት ሲታደግ ግን ለመጀመሪያ ጊዜው ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት ሲሽከረከር የሚታየው የተንቀሳቃሽ ምስል ላይ በአንድ አውራ ጎዳናው በምሽት በጎኑ ለወደቀው ኤልሞሌ፣ የዝሆን ልጅ፣ ግለሰቡ የሁለት እጅ መዳፎቹን አቆላልፎ ደረቱን ሲጫን ይታያል።

ከአስር ደቂቃ በኋላም ዝሆኑ ተነስቶ ቆመ።

የዝሆኑ ልጅ፣ ኤልሞሌ፣ በምሥራቃዊ ታይ የቻንታቡሪ አውራጃ ከሌሎች በርካታ ዝሆኖች ጋር አውራ ጎዳናውን እያቋረጠ ነበር።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የማና ባልደረቦች ዝሆኑን ገጭቶ የተዘረረውን የሞተር ብስክሌቱን አሽከርካሪ ሲረዱ ይታያል።

አሽከርካሪው ለወሬ የሚበቃ ጉዳት አልደረሰበትም ተብሏል።

ማና ላለፉት 26 ዓመታት በነፍስ አድን ሠራተኝነት ማገልገሉን፣ አደጋው ስፍራ የደረሰው ከሥራ ሠዓቱ ውጪ እየተንሸራሸረ ባለበት ወቅት እንደሆነ ለሮይተርስ ገልጿል።

"ሕይወትን ማትረፍ በደመነፍሴ ውስጥ ያለ ነገር ነው። ነገር ግን የኤልሞሌውን ሕይወት ለማትረፍ በምጥርበት ሰዓት ሁሉ ጭንቀት ውስጥ ነበርኩ። ምክንያቱም እናቱ እና ሌሎች የመንጋው አባላት ሲጠሩት ይሰማኝ ነበር" ሲል ለዜና ወኪሉ በስልክ አስረድቷል።

አክሎም "የዝሆኑ ልብ የት ስፍራ ሊገኝ እነደሚችል በአንድ የኢንተርኔት ቪዲዮ ላይ ባየሁት እና በሰው ልጅ አፈጣጠር ላይ ተመስርቼ ገምቻለሁ፣ ኤልሞሌው መንቀሳቀስ ሲጀምር እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም" ብሏል።

ኤልሞሌው ወደ እናቱ እና ሌለች የመንጋው አባላት ከመመለሱ በፊት ለአስር ደቂቃ ያህል ከቆመ በኋላ ተጨማሪ ሕክምና እንዲያገኝ ወደ ሌላ ሥፍራ ተወስዶ ነበር ሲል የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ኤልሞሌው ከእናቱ እና ከመንጋው ጋር በሰላም መቀላቀሉም ተሰምቷል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኛው ማና ደግሞ ኤልሞሌው መተንፈስ እንዲችል የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ የሰጠው ብቸኛው እንስሳ መሆኑን ተናግሯል።

ኤልሞሌው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ከተሰጠው በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኤልሞሌው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ከተሰጠው በኋላ