በአዲስ አበባ የእጅ ቦምብ ፈንድቶ የሦስት ሰዎች ህይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, ADDIS ABABA POLICE
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የእጅ ቦምብ ፈንድቶ በሰው ህይወትና በአካል ላይ ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።
አደጋው የደረሰው ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ዛሬ እሁድ ታኅሳስ 11/2013 ዓ.ም ሲሆን በፍንዳታው የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉንና አምስት ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ኮሚሽኑ በፌስቡኩ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ እንዳመለከተው ቦምቡ የፈነዳው ጠዋቱ 2፡30 በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ስልጤ መስጊድ ጀርባ አካባቢ ለልማት በፈረሰ ክፍት ቦታ ላይ መሆኑን አመልክቷል።
ጉዳቱ የደረሰው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በስፍራው ተጥሎ በተገኘው የእጅ ቦምብ አማካይነት ሲሆን፤ በፍንዳታው የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ ገልጿል።
በቦምቡ ፍንዳታ ህይወታቸው ከጠፋው ሰዎች በተጨማሪ በአምስት ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንም ኮሚሽኑ አረጋግጧል።
ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ያለው የምርመራ ሂደት እየተጣራ መሆኑንም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ ገልጸዋል።
ጨምረውም በፍንዳታው ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ እንደተጠናቀቀ ውጤቱ ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚሆንም አመልክተዋል ።
በተለያዩ ቦታዎች እንደ አልባሌ በሚጣሉ ቦምቦችና ፈንጂዎች የንፁሃን ህይወት እየተቀጠፈ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ኅብረተሰቡም አጠራጣሪ ነገሮች ሲገጥመው ከመንካት እንዲቆጠብና ለፀጥታ አካላት እንዲጠቁም ጠይዋል።
ከሳምንታት በፊት በተመሳሳይ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ አድዋ ድልድይ አካባቢ ተጥሎ የነበረ የእጅ ቦምብ ፈንድቶ በሰው ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።












