የኢስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አምብሮሴ ድላሚኒ በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ አራት ሳምንታት በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቅ።
ኢስዋቲኒ የስዋዚላንድ አዲሱ ይፋዊ መጠሪያ ነው።
መንግሥት እንዳስታወቀው የ52 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ነው ዕሁድ ዕለት ሕይወታቸው ያለፈው።
ምንም እንኳን ለሞታቸው ምክንያት ምን እንደሆነ በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮሮረናቫይረስ ከተያዙ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነበር ተብሏል።
የቀድሞዋ ስዋዚላንድ የአሁኗ ኢስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በስልጣን ላይ ነበሩ።
በደቡባዊ አፍሪካ የምትገኘው ትንሿ ኢስዋቲኒ በዓለማችን ላይ ሙሉ በሙሉ በንጉሳዊ አስተዳደር ከሚተዳደሩ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ስትሆን አንድ ሚሊየን የሚደርስ የሕዝብ ቁጥር አላት።
እስካሁንም 6 ሺ 768 ሰዎች በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 127 ሰዎች ደግሞ ከዚሁ ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አምብሮሴ ድላሚኒ በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው የተነገረው ባሳለፍነው ወር ነበር። በወቅቱም ''የተለመዱ የቫይረሱን ምልክቶች እያሳየሁ አይደለም ጤንነቴም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል'' ብለው ነበር።
ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል መዘዋወራቸውንና ከሕመማቸው እያገገሙ መሆኑን መንግሥት አስታውቆ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ ስዋዚላንድ 50ኛ ዓመት የነፃነት በዓል በምታከብርበት ዕለት ነበር ንጉስ ምስዋቲ ሦስተኛ የሃገራቸውን የስም ለውጥ ያስታወቁት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ለ82 ዓመታት በንግሥና የቆዩት የንጉስ ሶብሁዛ ልጅ የሆኑት ንጉሥ ምስዋቲ በአሁኑ ወቅት 15 ሚስቶች አሏቸው። እንደ ንጉሡ የህይወት ታሪክ ፀሃፊዎች መረጃ ከሆነ የአሁኑ ንጉሥ አባትም በዙፋናቸው በቆዩበት ዘመን 125 ሚስቶች ነበሯቸው።
'ንግዌንያማ' ወይም 'አንበሳው' ተብለው የሚታወቁት ንጉሡ ባሏቸው በርካታ ሚስቶችና በሚያዘወትሩት ባህላዊ ልብስ ይታወቃሉ።
የኢስዋቲኒ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ በማድረግና በሴቶች ላይ በሚፈፀም አድልዖ ምክንያት በሰብአዊ መብት ተሟጋቾ ይወቀሳል።












