ከምርጫ በኋላ በተከሰተ ነውጥ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የኬንያ መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ታዘዘ

የኬንያ የምርጫ ነውጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያው ከፍተኛ ፍርድ ቤት አወዛጋቢ የተባለውን በአውሮፓውያኑ 2007-2008 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተከሰተው ነውጥ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ወስኖበታል።

መንግሥት ሴቶቹን ፆታዊ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መከላከል አልቻለም ሲልም ነው 30 ሺህ ዶላር ለእያንዳንዳቸው፣አራት ሴቶች እንዲከፈል ብይኑን የሰጠው።

ውሳኔው ትልቅ ስኬት የተባለ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች የሰብዓዊ መብት ቡድን ኃላፊ ናይቶር ኒያሙ ማታንጌ በመጨረሻም ፍትህ ተገኘ ብለዋል።

ቡድኑ የፍርድ ሂደቱንም ሲደግፍ ነበር።

ኃላፊዋ በውሳኔው የተሰማቸውን ደስታ ቢገልፁም መንግሥት እንዲህ አይነት ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ ኃላፊነቱን ቀድሞ ሊወጣ ይገባል በማለት አሳስበዋል።

ዳኛ ዌልደን ኮሪር በበኩላቸው ሴቶቹ ጥቃት ሲደርስባቸው የመኖር መብታቸው ተጥሷል፤ የእኩልነት መብት ተነፍጓቸዋል ብለዋል።

መንግሥት ከጥቃት፣ ከእንግልትና ፣ ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ከመዋረድ ሊጠብቃቸው አልቻለምም ብለዋል ዳኛው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች ምርጫውን ተከትሎ በተነሳው ነውጥ 1 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል፤ 500 ሺህ ሰዎም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ሴቶችም ተደፍረዋልም ተብሏል።

የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ምዋይ ኪባኪ ምርጫውን አሸንፈዋል በሚልም ነው ተቃውሞው የተቀጣጠለው።

የፕሬዚዳንቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል ብለዋል።

የወቅቱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምዋይ ኪባኪን ሲደግደፉ፣ የአሁኑ የሳቸው ምክትል ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ደግሞ የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊ ነበሩ።

በጊዜውም ግጭቱን አቀጣጥለዋልም በሚል በሰብዓዊነት ላይ በሚደርስ ወንጀል በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተከሰው ነበር። ሁለቱም ወንጀሉን የካዱ ሲሆን በኋላም ክሱ ውድቅ ተደርጓል።