በእንጆሪ ጣዕም የተዘጋጀ የፀረ-ኤችአይቪ መድኃኒት ለአፍሪካውያን ህፃናት ሊቀርብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዋጋው ረከስ ያለና የእንጆሪ ጣዕም የተጨመረበት የፀረ-ኤች አይ ቪ ህክምና ወይም አንቲ- ሪትሮቫይራል ቴራፒ መድኃኒት በአፍሪካ ላሉ ህፃናት ሊቀርብ መሆኑን የእርዳታ ድርጅቶች አስታወቁ።
በመጪው አውሮፓውያኑ ዓመትም በአፍሪካ ውስጥ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል።
ይህም መድኃኒት ጄኔሪክ ተብሎ የሚጠራውና በተመጣጣኝ ዋጋ ገበያ ላይ በሚውሉ የመድኃኒቶች አይነትም ለህፃናት የቀረበ የመጀመሪያው የፀረ- ኤችአይቪ ህክምና፣ አንቲ- ሪትሮቫይራል ቴራፒ መድኃኒቶች እንደሆነም ተገልጿል።
በዓለም ላይ 1.5 ሚሊዮን ህፃናት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚገምት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ግማሹ ብቻ ናቸው ህክምና እያገኙ ያሉት ብሏል።
በተለይም ከፀረ-ኤችአይቪ ሕክምና ጋር ተያይዞ ለህፃናት ዋነኛው ፈታኝ ነገር ሆኖ የቆየውም የእነዚህ የአንቲ- ሪትሮቫይራል ቴራፒ እንክብሎች ጣዕም መራራ መሆን ነው።
በዚህመ ሳቢያ ቫይረሱ ያለባቸው ህፃናት መድኃኒቶቹ በመምረራቸው ምክንያት ሳያቋርጡ እንዲወስዱ ማድረግን አዳጋች አድርጎታል።
ከዚህም በተጨማሪ የእንክብሎቹን ጣዕም መቀየር ብቻ ሳይሆን መጠናቸውም ለህፃናቱ በሚስማማ መልኩ ሆነው እንደሚመረቱም የጤና ባለሙያዎች አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ለአዋቂዎች የተዘጋጁትን የጸረ ኤችአይቪ ህክምና (አንቲ- ሪትሮቫይራል ቴራፒ) እንክብሎችን በመስበር ለህፃናት ይሰጥ የነበረውን አሰራርም ያስቀራል ትብሏል።
በተጨማሪም መድኃኒቱን ለማቅረብ ሌላው እክል ሆኖ የነበረው የዋጋው ሁኔታም በቅርብ ዓመታት ውስጥ መሻሻል ቢያሳይም ለብዙዎች የማይቀመስ ሆኖ ቆይቷል።
በፊት 500 ዶላር በዓመት ያስወጣ የነበረው የፀረ ኤችአይቪ ህክምና (አንቲ- ሪትሮቫይራል ቴራፒ) መድኃኒት በአዲሱ ዋጋ መስረት ወደ 120 ዶላር በዓመት ወርዷል።
በቅርብ ወራትም ውስጥ በቤኒን፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ናይጄሪያና ዚምባብዌ የሚገኙ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ህፃናት መድኃኒቱ ይደርሳቸዋል ተብሏል።












