ኮቪድ-19፡ የዓለማችን ትልቁ የፕላስቲክ ጓንት አምራች ድርጅት ፋብሪካዎቹን ሊዘጋ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለማችን ትልቁ የፕላስቲክ ጓንት አምራቹ 'ቶፕ ግላቭ' ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ፋብሪካዎቹን እንደሚዘጋ አስታወቀ።
ድርጅቱ ይህን ያለው 2500 የሚሆኑ ሠራተኞቹ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ ነው።
ንብረትነቱ የማሌዥያ የሆነው 'ቶፕ ግላቭ' ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሲባል 28 ማምረቻዎቹን ተራ በተራ ይዘጋል ተብሏል።
ፋብሪካዎቹ መቼ መዘጋት እንደሚጀምሩ የታወቀ ነገር ባይኖርም ደረጃ በደረጃ ለመዝጋት መታቀዱ ተገልጿል።
ድርጅቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የበሽታው መከላከያ ግብዓት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮለት ነበር።
ይሁን እንጅ በሚተማመንባቸው ዝቅተኛ ተከፋይ ስደተኛ ሰራተኞቹ የሥራ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ስጋቶች ነበሩ።
ሰኞ ዕለት የማሌዥያ የጤና ሚኒስተር የቶፕ ግላቭ ፋብሪካዎች እና የሰራተኞች መኖሪያ በሚገኙበት አካባቢው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስርጭት መጨመሩን አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎ 5 ሺህ 800 ሰራተኞች እስካሁን የተመረመሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 2 ሺህ 453ቱ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ብሏል።
ቶፕ ግላቭ በማሌዥያ 41 ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን አብዛኞቹ ሰራተኞቹ ከኔፓል የመጡና በተጨናነቁ የመኖሪያ ህንፃዎች የሚኖሩ ናቸው።
"በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ሆስፒታል ገብተዋል። የቅርብ ንክኪ ያላቸውም ራሳቸውን ለይተዋል" ሲሉ የጤና ሚኒስቴር ዳሬክተር ጀነራል ኑር ሂሻም አብዱላህ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ቶፕ ግላቭ በዚህ ዓመት በዓለማችን ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገብ በዓለም ትኩረት ውስጥ ቆይቷል፤ በዚህ ብቻም ሳይሆን በሰራተኞች የጉልበት ብዝበዛ ክሶችም የዓለም ዋነኛ ትኩረትም ሆኗል።
ሐምሌ ወር ላይ አሜሪካ የሰራተኞች የጉልበት ብዝበዛን ምከንያት በማድረግ ከሁለት የድርጅቱ ቅርንጫፎች ጓንቶች እንዳይገቡ አግዳለች።
የአሜሪካ የሰራተኛ መሥሪያ ቤት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርትም ተመሳሳይ ሃሳብ አንስቷል።
መስከረም ወር ላይም ስደተኛ ሰራተኞች ለሎስ አንጀለስ ታይምስ በቶፕ ግላቭ ፋብሪካዎች ያለውን የሥራ ሁኔታ አስቸጋሪነት ተናግረዋል። ስደተኞቹ በሳምንት 72 ሰዓታት እንደሚሰሩና ዝቅተኛ ክፍያ እንደሚከፈላቸውና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ነበር ለሎስ አንጀልስ ታይምስ ያስረዱት።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላም ድርጅቱ ከገለልተኛ አማካሪው በተሰጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት ለሰራተኞቹ የቅጥር የማካካሻ ክፍያ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቆ ነበር።
የማሌዥያ የፕላስቲክ ጓንት አምራቹ ቶፕ ግላቭ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ኮንዶም፣ የፕላስቲክ ድድ እንዲሁም ሌሎችን ምርቶችን በማምረት ይታወቃል።












