አልጄርያውያን የፕሬዘዳንት የሥልጣን ዘመንን ለመገደብ ሕዝበ ውሳኔ እያካሄዱ ነው

አልጄርያውያን ሕዝበ ውሳኔ እያካሄዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP

አልጄርያውያን ሕዝበ ውሳኔ እያካሄዱ ነው። ለዘመናት አገሪቱን የመሩት ፕሬዘዳንት አብዱላዚዝ ቡተልፊካ አምና ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ የታየውን ለውጥ ዘላቂ የሚያደርግ ምርጫ እንደሚሆንም ይታመናል።

ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄደው ጥቅምት 1 ሲሆን፤ ቀኑ እአአ በ1954 አልጄሪያ ከፈረንሳይ ነጻነቷን ለማግኘት ትግል የጀመረችበት ወቅት መታሰቢያ ነው።

ፕሬዘዳንት አብደልመጂድ ተቦኔ ለህክምና ጀርመን ተወስደዋል። ህመማቸው ምን እንደሆነ ባይገለጽም የቅርብ ባልደረቦቻቸው ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው በኋላ አልጀርስ በሚገኝ ወታደራዊ ሆስፒታል ራሳቸውን አግልለው ቆይተዋል።

አልጄርያውያን ሕዝበ ውሳኔ የሚያካሂዱት የፕሬዘዳንት የሥልጣን ዘመን ለመገደብ እና ጸረ ሙስና ተቋም ለመመስረት ነው። ውጤቱም ነገ ይፋ ይደረጋል።

ሕዝበ ውሳኔው ለምን በዚህ ወቅት ተካሄደ?

የ74 ዓመቱ ፕሬዘዳንት አብደልመጂድ ተቦኔ ወደ ሥልጣን የመጡት አምና የተካሄደውን አወዛጋቢ ምርጫ ተከትሎ ነው። የቀድሞው ፕሬዘዳንት አብዱላዚዝ ቡተልፊካ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ ሲያስታውቁ በአገሪቱ ተቃውሞ ተነስቶ ከቦታቸው መነሳታቸው ይታወሳል።

ፕሬዘዳንት አብደልመጂድ “አዲስ አልጄርያን እንመሰርታለን” ሲሉ ቃል ገብተዋል። በቡተልፊካ አስተዳደር የነበረውን የፖለቲከኞች እና ነጋዴዎች አሻጥር እንደሚያስወግዱም ተናግረዋል።

አዲሱ አስተዳደር ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ለውጥ ለማምጣት ደግሞ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ማሻሻል የግድ ነው።

ለውጡ ምንድን ነው?

የአልጄርያ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ሕዝቡ ድምጽ ከሰጠ አንድ ፕሬዘዳንት ሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ ነው መምራት የሚችለው። የሕዝብ እንደራሴዎችም ከሁለት ዘመን በላይ ተወካይ ሆነው መቆየት አይችሉም።

ቡተልፊካ፤ 2008 ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ሲነሱ ሕገ መንግሥቱን ለውጠውት ነበር።

ሌላው ለውጥ ጸረ ሙስና ተቋም መመስረት ነው። ቡተልፊካ ከሥልጣን እንዲወገዱ ካደረጉ ችግሮች አንዱ ሙስና መንሰራፋቱ ነበር።

የሚሻሻለው ሕገ መንግሥት ለሕዝብ ተቋሞች እውቅና የሚሰጥ፣ የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት የሚያከብር እንደሆነም ተገልጿል።

መንግሥት እና ተቺዎች ምን አሉ?

ጠቅላይ ሚንስትር አብዱላዚዝ ጀራርድ አዲሱ ሕገ መንግሥት “ከዓመታት መከፋፈል በኋላ አገራችንን ወደትክክለኛው አቅጣጫ ይመራል” ብለዋል።

ሕገ መንግሥቱ ላይ የሚደረገው ማሻሻያ “ሙሰኛውን መንግሥት የጣለውን” የሕዝብ ጥያቄ የሚመልስ እንደሆነም ተናግረዋል።

የቀድሞ ዳኛና የተቃዋሚ መሪ ዙቤይዳ አሱል በበኩላቸው፤ ሕዝበ ውሳኔው ተቃውሞውን ለማዳፈን ያለመ ነው ይላሉ።

‘ሂራቅ’ በሚል የሚታወቀውን የአልጄርያ አብዩት ጥያቄ ለማክሰም ሲባል ሕገ መንግሥቱን በአፋጣኝ ለማሻሻል እየተሞከረ እንደሆነም አክለዋል።

የፖለቲካ ምሁሯ ፕ/ር ሉዊሳ ድሪስ-አቲ ሀማዱቼ እንደሚናገሩት፤ የሂራቅ አባላት በማሻሻያው ስላልተሳተፉ የአዲሱ ሕገ መንግሥት ትክክለኛነት አጠያያቂ ነው።

በማሻሻያው እንዲሳተፉ የተደረገው ቀድሞ የነበሩ የሂራቅ አባሎች ናቸው። ቀዳሚዎቹ የሂራቅ አባላት አምና ምርጫ ሲካሄድ ከእንቅስቃሴው ወጥተዋል።

በኮቪድ-19 ሳቢያ ለሕዝበ ውሳኔው ቅስቀሳ የተደረገው በቴሌቭዥን፣ ራድዮና ማኅበራዊ ሚዲያ ነበር።

ምክር ቤት የሚገኙት ሁለት ትልልቅ ፓርቲዎች፤ ናሽናል ሊበሬሽን ፍሮንት እና ናሽናል ዴሞክራቲክ ራሊ፤ ሕዝበ ውሳኔውን ይደግፋሉ።

በሌላ በኩል ሂራቅ ወጥ መሪዎች ያሉት ንቅናቄ ባይሆንም በርካታ ተቃዋሚዎች ሕዝበ ውሳኔውን አይቀበሉም። ትክክለኛ ለውጥ ያመጣል ብለውም አያምኑም።

ዋነኛ የሙስሊም ፓርቲዎች የሆኑት ሶሳይቲ ፎር ፒስ፣ ሙቭመንት ፎር ጀስቲስ ኤንድአ ዴቨሎፕመንት እንዲሁም ዘ ናህዳ ሙቭመንት በበኩላቸው፤ ሕዝበ ውሳኔው የአልጄርያን የእስልምና ባህል የጠበቀ አይደለም ይላሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመብት ተሟጋቾች ጥምረት የሆነው ዴሞክራቲክ ኦልተርኔቲቭ ሕዝበ ውሳኔውን አይቀበሉትም። ጥምረቱ፤ አልጄርያ የሚያስፈልጋት ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ነው ይላል።