ፕሬዝዳንታዊ ተፎካካሪው በምርጫው ዋዜማ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዛንዚባር ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪው በቁጥጥር ስር እንደዋለበት አስታወቀ።
በታንዛኒያ ነገ አካባቢያዊ እና አገር አቀፍ ምርጫው ይካሄዳል።
ማሊም ሰይፍ ዛሬ ከጠዋት ላይ በምርጫ ጣቢያ በፖሊሶች ተከብበው መወሰደቻውን 'አክት ዋዛሌንዶ' ፓርቲ ገልጿል።
በታንዛኒያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ራይት በምርጫው ዋዜማ በዛንዚባር እና መላው ታንዛኒያ እየተከሰቱ ያሉ እስር፣ ግድያዎችና አመጽ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ፔምባ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ፖሊስ ሶስት ሰዎችን ገድሏል መባሉን ተከትሎ ፖሊስ ማስተባበያ አውጥቷል።
ዛንዚባር በታንዛኒያ ባህር ዳርቻዎች አካባቢ የሚገኙ የደሴቶች ስብስብ ስትሆን በከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር ናት።
የዛንዚባር ነዋሪዎች የደሴት መሪዎቻቸውን የሚመርጡ ሲሆን ይህ ደግሞ የዛንዚባርን ፕሬዝዳንትና በአጠቃላይ የታንዛኒያ ብሄራዊ ምርጫ ላይም እንዲሳተፉ ያደርጋቸዋል።
ምንም እንኳን ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲው መሪዬ በቁጥጥር ስር ውሎብኛል ቢልም ባለስልጣናት ግን በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። የፓምባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ እንደገለጹት ሰኞ ዕለት ፖሊስ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ለመግባት የሞከሩ ሰዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሞ ነበር።
ምክልት ኮሚሽነሩ ሲሞን ሲሮ አክለውም ''ፔምባ ውስጥ ሞተዋል የተባሉትን ሶስት ሰዎች ፖሊስ አልገደላቸውም'' ብለዋል። በተጨማሪም 42 ሰዎች ከተፈጠረው አመጽ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።
በርካታ የታንዛኒያ ነዋሪዎች ደግሞ በምርጫው ዋዜማ እንደ ዋትስአፕና ትዊተር ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችን መጠቀም እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው።
ማሊም ሰይፍ ዛሬ ከጠዋት ላይ በምርጫ ጣቢያ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉት የምርጫ ድምጻቸውን ለመስጠት በሚሞክሩበት ወቅት እንደሆነ ፓርቲያቸው ገልጿል።
በዛንዚባር ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ 17 ተፎካካሪዎች ይወዳደራሉ።












