አብን በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ከተሞች የጠራው ሠልፍ ተሰረዘ

NAMA

የፎቶው ባለመብት, NAMA

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች እና በአዲስ አበባ የጠራውን ሰልፍ መሰረዙን ለቢቢሲ አስታወቀ።

አብን "በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ዘር ማጥፋት የሚያወግዝ " የተቃውሞ ሰልፍ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች ጥቅምት 22 ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ ለማካሄድ ጥሪ አስተላልፎ እንደነበረ ይታወሳል።

የፓርቲው የሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የተጣራውን ሰልፍ መምራት ስለማንችል ሰልፉ ተሰርዟል" ብለዋል።

ዛሬ ጠዋት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስለ ሠልፉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ምክክር እያደረገ ሳለ በፖሊስ መከበቡን እና የፓርቲው አባላት ከቢሯቸው መውጣትም ሆነ መግባት አለመቻላቸውን አቶ ጣሂር መሐመድ ተናግረዋል።

"እንቅስቃሴያችንን ለመገደብ ሙከራ ተደርጓል። በዚህ ሁኔታ ሰልፉን መምራት ስለማንችል እንዲቀር ተወስኗል" ብለዋል።

"ዛሬ ጠዋት ስብሰባ እያደረግን ነበር። ከሰዓትም ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ጥሪ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ቢሯችን በፖሊስ ተከብቧል። መግባትም ሆነ መውጣት አልቻልንም፤ ጋዜጠኞችም ወደ ቢሯችን መግባት አልቻሉም" ያሉ ሲሆን ቢሯቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት መከበቡን ተናግረዋል።

"5፡30 ጀምሮ ተከብቧል። ጭምብል በለበሱ እና በኃይል በታጠቁ ፖሊሶች ነው የተከበብነው። እዚህ ደረጃ የሚያደርስ ነገር እንደሌለ ለፖሊስ አባላቱ ነግረናቸዋል። እነሱ ግን 'ታዘን ነው' ስለሚሉ ምንም ማድረግ አልቻልንም" ብለዋል።

ትናንት የአማራ ክልላዊ መንግሥት ነገ በክልሉ ከተሞች የተጠራው ሠላማዊ ሠልፍ ዕውቅና የለውም ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።

የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በማህበራዊ ሚዲያ የተጠራው ሠልፍ ክልሉ እንዲረጋጋ ለማይፈልጉ ኃይሎች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚመች ነው ብለው ነበር።

አቶ ግዛቸው "ችግሩን ሰልፍ በማድረግ ብቻ አይፈታም። ሰልፍ መፍትሔ ቢሆን የክልሉ መንግሥትም ገዢውን ፓርቲ በማስተባበር ሰልፍ በጠራ ነበር" ብለው ነበር።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ጉዳዩ የሚመለከተው ፌደራል ፖሊስን ነው ብለውናል።

የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ አቶ ጄይላን አብዲ በበኩላቸው "በስልክ መረጃ አልሰጥም" በማለታቸው ተጨማሪ መረጃ ሳናገኝ ቀርተናል።