ፊሊፒንስ፡ በእስር ላይ ያለችው እናቷ ጋር በግድ የተለያየችው ጨቅላ መሞት ቁጣን ቀሰቀሰ

ሬይና ሜ ናሲኖ ከጨቅላ ልጇ ሪቨር ጋር

የፎቶው ባለመብት, Kapatid

የምስሉ መግለጫ, ሬይና ሜ ናሲኖ ከጨቅላ ልጇ ሪቨር ጋር

በፊሊፒንስ በእስር ላይ ያለችው ፊሊፒናዊ እናት ጋር በግድ የተለያየችው ጨቅላ ህፃን መሞት በርካቶችን አስደንግጧል።

ጨቅላዋ የሶስት ወር ዕድሜ ያላት ስትሆን እናቷ "ከልጄ ጋር አትለያዩኝ" ብላ ብትማፀንም ሰሚ አላገኘችም ተብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነችው እናት ሬይና ማኤ ናሲኖ በቁጥጥር ስር በዋለችበትም ወቅት ነፍሰ ጡር መሆኗን አላወቀችም ነበር።

በመዲናዋ ማኒላ በቁጥጥር ስር ስትውልም ፖሊስ በድንገተኛ ሁኔታ በምሽት ሲሆን ከሷም ጋር የነበሩ ሁለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም እንዲሁ ለእስር ተዳርገዋል።

በእስርም ላይ እያለች ነው የ23 አመቷ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ነፍሰ ጡር መሆኗን ያወቀችው።

ልጇንም ከተገላገለች በኋላ በእስር ላይ እያለሽ ማሳደግ አትችይምም ተብላ አንድ ወር አለፍ እንዳለት ነው ሪቨር የሚል ስም የሰጠቻት ህፃኗን የተነጠቀችው።

ሁለት ወርም ሳይሞላት የህፃኗ ህይወት ማለፍም በእስር ላይ ያሉ እናቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ ውግዘትንም ከማስከተልም በተጨማሪ የፍትህ ስርአቱ ላይ ከፍተኛ ጥያቄን ፈጥሯል።

ሬይና ማኤ የከተማ ድህነትን ለመዋጋት ከሚሰራው ካዳማይ ከተባለው ቡድን ጋር የምትሰራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ናት።

ከአቻ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በቁጥጥር ስር በዋለችበት ወቅት ህገ ወጥ መሳሪያ ይዛችኋል በሚል ሲሆን ሶስቱም ክደዋል።

የመብት ተሟጋቾቹ እንደሚሉት ግራ ዘመም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ለማንበርከክ በመንግሥት የተወጠነ ሴራ ነው ይላሉ።

ምንም እንኳን በእስር ላይ ሆኖ ልጅ መውለድ ፈታኝ ቢሆንም እናትነትን በደስታ እንደተቀበለችው ጠበቃዋ ጆሳሊ ዴይንላ ይናገራሉ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ስጋት የፈጠረባት እናት እንዲሁም የፊሊፒንስ ብሔራዊ የጠበቆች ማህበር እንድትለቀቅ የጠየቁ ሲሆን እሷን ጨምሮ 22 የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ወስኖ ነበር።

ሆኖም በኋላ ውሳኔው ተቀልብሶ ከልጇ ጋር እስር ቤት እንድትቆይ ተወሰነ።

በፊሊፒንስ ህግ መሰረት በእስር ቤት የተወለዱ ህፃናት ከእናቶቻቸው ጋር መቆየት የሚችሉት አንድ ወር ብቻ በመሆኑም ከልጇ እንድትለያይ ተወሰነ።

ከልጇ እንዳይለዩዋት ብትማፀንም ሰሚ አላገኘችም። ህፃኗም በአያቷ እንክብካቤ ስር እንድትሆን ተወሰነ። የህፃኗ የጤንነት ሁኔታም ከቀን ወደቀን እያሽቆለቆለ የመጣ ሲሆን በከፍተኛ ተቅማጥ ትሰቃይ ነበር።

ሆስፒታልም ስትገባ የሳንባ ምች እንደተጠቃችም ታወቀ፤ ህክምና ቢደረግላትም ሁኔታዋ ከፍቶ ህይወቷ አልፏል። ጨቅላዋ ህይወቷ ከማለፉ በፊትም ልጇን እንድትጎበኝ ብትማፀንም ጥያቄዋ ተቀባይነት ሳያገኝም ቀረ፤ ልጇንም ሳታይ ቀረች።

በርካታ እስረኞች ልጆቻቸውን እንዲጠይቁ በሚፈቀድላቸው ሁኔታ የሷ እስር ፖለቲካዊ ስለሆነ ያልተፈቀደላት በሚልም በርካቶች ቁጣቸውን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ወስደውታል።

ለቀብሯም ሆነ ለኃዘንም ከእስር ቤት እንድትወጣ የተፈቀደላት ለሶስት ሰዓታት ብቻ ነው።