ፖሊሶች ከፈረስ ላይ በገመድ አስረው የወሰዱት ጥቁር አሜሪካዊ 1 ሚሊዮን ዶላር ይገባኛል ሲል ከሰሰ

ሁለት ነጭ ፖሊሶች በፈረስ ላይ ተቀምጠው በቴክሳስ ጎዳናዎች ላይ በገመድ አስረው የወሰዱት ጥቁር አሜሪካዊ

የፎቶው ባለመብት, Anonymous

ሁለት ነጭ ፖሊሶች በፈረስ ላይ ተቀምጠው በቴክሳስ፣ ጋልቭስቶን ጎዳናዎች ላይ በገመድ አስረው የወሰዱት ጥቁር አሜሪካዊ የከተማዋን አስተዳደርና ፖሊስን ከሷል። አንድ ሚሊዮን ዶላርም ይገባኛል ብሏል።

የ44 አመቱ ዶናልድ ኒሊ ያለ ፈቃድ የእግረኞች መረማመጃ ላይ ተኝቶ ተገኝቷል በሚል ወንጀልም ተጠርጥሮ በገመድ አስረው ፖሊሶች ሲወስዱት የታየው።

ይህም ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ፖሊስ ይቅርታ ጠይቆ ነበር።

በዚህ ሳምንት የቀረበው ክስ የሚያስረዳው ፖሊሶቹ የፈፀሙት ድርጊት" ፅንፈኛና አሰቃቂ ነው" በማለት ዶናልድ ኔሊም ለስነ-ልቦናዊ ቁስልና የአዕምሮ ጤንነቱም ላይ ጉዳት አድርሰውበታል ይላል።

ቤት አልባ የሆነው ዶናልድ በእግረኞች መረማመጃ ላይ ተኝቶ በመገኘቱም ነው ፖሊሶች በቁጥጥር ስር እንዳዋሉት የአሜሪካ ሚዲያዎች የዘገቡት።

ፖሊስ ፍቃድ የሌለው ቦታ ላይ ተገኝቷል ብሎ ያቀረበበትም ወንጀል ፍርድ ቤቱ በነፃ አሰናብቶታል።

በገመድም ታስሮ ሲወሰድ ያዩ በርካቶችም ከባርነት ዘመን ጋርም በማነፃፀር ቁጣቸውን ገልፀዋል።

በክሱም ላይ ይሄው ሁኔታ ተገልጿል።

ክሱ እንደሚያትተውም " በገመድ ታስሮ በጎዳናዎች ላይ ባርያ ይመስል መውሰድ አፀያፊ ነው" ይላል።

የከተማዋን እንዲሁ የጋልቭስቶን ፖሊስን ተጠያቂ ያደረገው ክሱ ዶናልድ በታሰረበት እጅ ሰንሰለት ምክንያት ጉዳት ደርሶበታል፤ በጎዳናው ላይ ይዘውትም ሲሄዱ በከፍተኛ ሙቀት ተለብልቧል እንዲሁም በሁኔታውም ፍርሃትና ውርደት እንደደረሰበትም ያትታል።

የከተማው አስተዳዳሪዎች ለሚዲያዎች አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በመጀመሪያ ዶናልድ በገመድ ታስሮ ሲወሰድ የሚያሳየው ምስል መውጣቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ቁጣ በገመድ አልታሰረም በማለት ፖሊስ ለማስተባበልም ሞክሮ ነበር። ከምርመራ በኋላ የወጣው ቪዲዮ እንደሚያሳየውም ፖሊሶች በዚህ መንገድ አስረው በማዋረዳቸውም ሲዘባበቱበት ተሰምተዋል።

የጋልቭስተን ፖሊስረ ኃላፊ ቬርኖን ሃሌ እንዳሉም በዚህ መንገድ ተጠርጣሪዎችን መውሰድ በአንዳንድ ሁኔታዎች ተቀባይነት ያለው ቢሆንም "በዚህ ወቅት ግን ፖሊሶቹ ያልተገባ ባህርይ ነው ያሳዩት" በማለት ተችተዋል።

ይህንን ለመፈፀም "የተደበቀ ሴራ አልነበረም" ያሉት ኃላፊው ዶናልድ ለደረሰበት "አላስፈላጊ ውርደት" ይቅርታ ጠይቀዋል።

ያንንንም ተከትሎ በዚህ መንገድ ተጠርጣሪዎችን ማሰር አይገባም በሚልም እግድ ተጥሎበታል።