ጣልያን፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጣልያናዊውን ታዳጊ ቅዱስ ለማለት ጫፍ ደርሳለች

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ስነ ስርአት

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ኢንተርኔትን በመጠቀም ስለ እምነቱ ቀናኢነት የሰበከው ጣልያናዊው ታዳጊ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የቅድስና ማእረግ ሊሰጠው እንደሆነ ተጠቁሟል።

ታዳጊው ካርሎ አኩቲስ በጎሮጎሳውያኑ 2006 ነው በሉኬሚያ ካንሰር ህይወቱ ያለፈው፤ ገና የአስራ አምስት አመት ታዳጊም ነበር።

ከመሞቱም በፊት "የኢንተርኔቱ ቅዱስ" የሚል ስያሜን አግኝቶም ነበር።

ቅዳሜ እለትም አሲሲ በተባለችው ከተማ በነበረው የቤተ ክርስቲያኗ ስርአትም ወደ ቅድስና ማዕረግ የሚያስጠጋው አንድ ደረጃን ያለፈ ስርአትም ተካሂዷል ተብሏል።

በርካታ ተአምራቶችን በኢንተርኔት (በይነ መረብ) ያካሂድ የነበረ ሲሆን የተለያዩ የካቶሊክ እምነት ድርጅት ድረገፆችንም ያግዝ ነበር።

አኩቲስ የአንድ ብራዚላዊ ልጅን ህይወት በተአምራዊ ሁኔታ ታድጓል በሚልም ነው ቫቲካን የቅድስና ማእረግን ልትሰጠው ያሰበችው።

ይህ ተአምራዊ ፈውስ የተፈጠረውም አኩቲስ ከሞተ በኋላ፣ በጎሮጎሳውያኑ 2013 ነው።

አኩቲስ ከሰማይ በመውረድም ልጁን ከጣፊያ ህመሙ ፈውሶታል ትላለች የካቶሊክ ቤተክርስቲያን።

አሁን ባለንበት ጊዜም ወደ ቅድስና ማዕረግ የተጠጋው ትንሹ ታዳጊም ሆኗል።

ቅዳሜ እለት ቅዱስ ፍራንሲስ ቤተ ክርስቲያን በነበረውም ስነ ስርአት የአኩቲስ ምስል የተገለጠ ሲሆን የተሰበሰቡትም ላደረገው ሰብዓዊ እርዳታ ምስጋናን ችረውታል።

አኩቲስ ቅዱስ ለመባል ቫቲካን በስሙ ሁለተኛ ተአምር ማረጋገጥ የሚኖርባት ቢሆንም የካቶሊክ ፖፕ ፍራንሲስ ግን የዚህን መስፈርት አስፈላጊነት በበርካታ አጋጣሚዎች አስቀርተውታል።

አኩቲስ ከጣልያን ቤተሰቦቹ በለንደን ቢወለድም ያደገውም ሆነ ህይወቱንም ያሳለፈው በጣልያኗ ሚላን ከተማ ነው።

በህፃንነቱ ቅዱስ ለሆነ ነገር ትልቅ ስፍራ ይሰጥ የነበረ መሆኑን እናቱ አንቶኒያ ሳልዛኖ ለኮሪ ዴላ ሴራ ጋዜጣ ተናግረዋል።

በብዙዎች ዘንድ የኮምፒውተር 'ጂኒየስ' (ልሂቅ ) የሚል ስያሜ የተሰጠው ታዳጊ ራሱንም ኮምፒውተር በህፃንነቱ አስተምሮም እምነቱን ለማስተማርና በርካታ የእምነት ድርጅቶችንም በመርዳት ይጠቀምበት ነበር።

ታዳጊው በበርካታ የእርዳታ ድርጅቶችም ተሳትፎ የነበረው ሲሆን ከራሱም ኪስ አውጥቶ አቅመ ደካሞችን ይረዳም ነበር።

"ባጠራቀማት ገንዘብ ቤት ለሌላቸው አቅመ ደካሞች ፍራሽና ብርድ ልብስ ይገዛ ነበር። ሲመሽም ትኩስ መጠጦችንም ይወስድላቸው ነበር" በማለት እናቱ ለካቶሊክ የዜና ወኪል ተናግራለች።

ካርሎ አኩቲስ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ቅዱስ/ ቅድስት ለመሆን መስፈርቶቹ ምንድንናቸው?

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሰረት የቅድስና ማዕረግ ለመቀበል አንድ ሰው ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ።

ከነዚህም ውስጥ፦

  • የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ

አብዛኛውን ጊዜ የቅድስና ማዕረግ የሚሰጠው ሰው ከሞተ ከአምስት አመታት በኋለ ነው። ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ፖፑ ሊሽሩት ይችላሉ።

  • የአምላክ ባርያ መሆን

ግለሰቧ/ ግለሰቡ/ በህይወት ዘመናቸው በምን ያህል ቅድስና ኖረዋል የሚለው ምርመራ ይካሄዳል፣ መረጃዎችም ይሰባሰባሉ። ጉዳዩም ተቀባይነት ካገኘ "የአምላክ ባርያ" ተብለው ይጠራሉ።

  • የጀግንነት እሴቶችን ማሳየት

የተሰበሰቡትን መረጃዎችም ተሰብስበው ግለሰቦቹ ምን ያህል የጀግንነት እሴቶችን አሳይተዋል የሚለውንም የሚገመግም አካል ያለ ሲሆን በዚህም አካል አማካኝነት ለፖፑ ይቀርባል።በዚህም ወቅት "ልበ ስሱ" ተብለው ይጠራሉ።

  • ተአምር ማረጋገጥ

በዚህ ደረጃ ላይ የደረሱ ግለሰቦች በስማቸው እንድ ተአምር ሊመዘግብላቸው ይገባል። ክስተቶች ተአምር ለመሆናቸው ማስረጃ ቀርቦባቸው ተመርምረው መረጋገጥ አለባቸው። በዚህም ወቅት እጩው ቅዱስ "የተባረከ/ የተባረከች" የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል።

  • የቅድስና ማዕረግ

የመጨረሻው ቅዱስ/ ቅድስት ተብሎ ማዕረግ ለመስጠት በስማቸው ሁለተኛ ተአምር መከወን ይኖርበታል።