ኤሚ ቤሬት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሊሆኑ ይችላሉ ተባለ

ኤሚ ቤሬት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኤሚ ቤሬት

ዳኛ ኤሚ ኮኒ ቤሬት በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ተደርገው ሊሾሙ መሆነ ተነገረ።

ፕሬዝደንት ትራምፕ እጩዋን ኤሚ ቤሬት ዛሬ በዋይት ሃውስ በሚካሄድ ስነ-ስርዓት ይፋ እንደሚያደርጉ ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

ኤሚ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ሩት ባደር ጊንስበርግን ይተካሉ።

ኢቢኤስ በርካታ ምንጮቹን በመጥቀስ እንደዘገበው ከሆነ ትራምፕ ከቀረቡላቸው በርካታ እጩዎች መካከል ዳኛ ቤሬት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ እንዲሆኑ ወስኗል ሲል ዘግቧል።

ትራምፕ ግን ትናንት ቅድሚያ የሰጡት እጩ ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

“ማን እንደሚሾም ነገ ታውቃለችሁ። ሁሉም ጠንካራ ናቸው። ከመካከላቸው አንዳቸው ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል ትራምፕ።

ዳኛ ቤሬት በትራምፐ የሚመረጡ ከሆነ ከአጠቃላይ 9 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል የወግ አጥባቂ ዳኞ ብዛት ወደ 6 ከፍ የሚል ይሆናል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ሆነው የሚሾሙ ዳኞች ሙሉ የዕድሜ ዘመናቸውን ማገልገል ይችላሉ።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያስተላለፉት ውሳኔም በአገሪቱ ፖሊስ እና ስትራቴጂዎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በሁሉም 50 የአሜሪካ ግዛቶች የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን መፍቀድ እና ትራምፕ አስተላልፈው የነበረውን የጉዞ ገደብ ማስቆም ተጠቃሽ ናቸው።

ኤሚ ኮሬት ቤሬት ማን ናቸው?

የ48 ዓመቷ ዳኛ ጠንካራ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በጻፉት ጽሑፍ ላይ የሰው ልጅ ህይወት የሚጀምረው ከተጸነሰበት ቅጽበት ጀምሮ ነው ብለዋል።

ይህ የዳኛዋ አቋም በአሜሪካ ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊ መሆኑ እንዲቀር በሚሹ ሰዎች ዘንድ ተስፋን አሳድሯል። እአአ 1973 ላይ በአሜሪካ ጽንስ ማቋረጥ በሕግ ተፈቅዷል።

ኢንዲያና ግዛት ውስጥ ከሚገኘው ኖተር ዳም ዩኒቨርሲቲ በሕግ የተመረቁት ዳኛ የትራምፕ ጠንካራ የስደተኞች ፖሊስ ደጋፊ መሆናቸው ይነገራል።

አሜሪካውያን የጦር መሳሪያ የመታጠቅ መብት አላቸው የሚል ጽኑ አቋም እንዳላቸውም ይገለጻል።

የ7 ልጆች እናት የሆኑት ኤሚ ቤሬት በተማሩበት ዩኒቨርሲቲም ለ15 ዓመታት አስተምረዋል።