ሩት ባደር ጊንስበርግን ማን ይተካቸው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩት ባደር ጊንስበርግ ሞት ዜና በአሜሪካ ታሪክ አንድ ታዋቂ የሮክ ዘፋኝ አልያም የሆሊዉድ ተዋናይ ሲሞት የሚታይ አይነት ምላሽን ነው ያስከተለው።
87 ዓመት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛዋ ሙሉ እድሜያቸውን ሕግን በማጥናትና በማስፈጸም ነው ያሳለፉት።
''ልቤ ተሰብሯል'' ብላለች እውቋ አቀንቃን ጄኒፈር ሎፔዝ። ''ምሳሌ መሆን የቻለች፤ ሮል ሞዴል እና ታጋይ ሴት አጥተናል'' ብላለች ሞዴልና ተዋናይውዋ ካራ ዴልቪኝ።
አክላም '' ወደዚህ ዓለም ላመጣሽው ነገር በሙሉ ምስጋና ይገባሻል'' ብላለች።
"የአንቺ ተጽዕኖ እና ስራ መቼም ቢሆን አይረሳም'' ያለችው ደግሞ ተዋናይዋ ፕሪያንካ ቾፕራ ናት።
በርካታ አሜሪካውያን በሞታቸው ሀዘናቸውን እየገለጹ ሲሆን አብዛኛዎቹም የማስታወሻ አበባዎችን በመላው አገሪቱ በሚገኙ ቦታዎች በስማቸው አስቀምጠዋል።
በዛሬው እለት ደግሞ አስከሬናቸው በዩኤስ ካፒቶል ህንጻ ያረፈ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነዋል።።
የሩት ባደር ጊንስበርግ ሞት በአሜሪካ ብዙ መነጋገሪያ ሆኗል። ሕይወታቸውን ሙሉ ለሴቶች እኩልነትና ለሕግ መከበር መስራታቸው ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላ ማነው የሚተካቸው የሚለው ጥያቄም ጭምር ብዙ ክርክሮችን አስነስቷል።
ለበርካታ ዓመታት በአሜሪካ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛነት ያገለገሉት ሩት ባደር ጊንስበርግ በሰማኒያ ሰባት ዓመታቸው ነበር በካንሰር ህመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።
ሩት ባደር ጊንስበርግ ከአውሮፓውያኑ 1993 ጀምሮ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኝነት የሰሩ ሲሆን ለሃያ ሰባት ዓመታት ያክል ሲያገለግሉ ቆይተው ነው በስራ ላይ እያሉ ነው ሕይወታቸው ያለፈው።
ከዚህ በፊት ሁለት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ለሾሙት ለፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ፕሬዚደንታዊ ምርጫው ሊካሄድ አጠር ያለ ጊዜ በቀረበት በዚህ ወቅት የሩት ባደር ጊንስበርግ ሞት ሶስተኛውን በመሾም በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የወግ አጥባቂ ዳኞችን የበላይነት ለማጠናከር ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚችልም ተነግሯል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት የጊዜ ገደብ የሌለው የዕድሜ ልክ ሹመት ሲሆን ባሁኑ ጊዜ አምስቱን አብላጫ ወንበር የያዙት ወግ አጥባቂ ዳኞች ናቸው።
በአሜሪካ የጽንስ ማቋረጥ መጻኤ ተስፋ፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ፣ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር እና የጤና አገልግሎት ጉዳዮች እሳቸው በማን እን እንዴት ይተካሉ ሚለው ጥያቄ ላይ የተንጠለጠለ ነው።
በሰማንያዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሆነው የሕግ መተግበሪያ መጽሀፍ የጻፉ የመጀመሪያዋም የሕግ ሙያ ቁንጮ ላይ የተቀመጡ ግለሰብ ናቸው።
ሩት ባደር ጊንስበርግ ነገሮችን ከበድ ባለ መንገድ ማድረግ የመረጡት ወደው ሳይሆን ገና ከጅምሩ ተገደው ነው።
ምንም እንኳን በታዋቂዎቹ ሀርሻርድ ዩኒቨርሲቲ እና ኮሎምቢያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ቢከታተሉም በአውሮፓውያኑ 1959 በከፍተኛ ውጤት ሲመረቁ ምንም አይነት ስራ ማግኘት አልቻሉም ነበር።
ሩት ባደር ጊንስበርግ ለሴቶችና ለአናሳ ቡድኖች መብት እድሜ ዘመናቸውን በመታገላቸው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተከታዮችና አድናቂዎች እንዲያፈሩ አድርጓቸዋል።
በመጀመሪያ የስራቸው ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ ሕገመንግስት ጾታን መሰረት ያደረገ ማግለልና መድልዎ ህገወጥ አንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ተጫውተዋል።
ነገር ግን ከህግ ጋር በተያያዘ ብቻ በሰሩት ስራ አይደለም በርካቶች የሚያደንቋቸውና የሚወዷቸው። ከዚህ በተጨማሪ ቆፍጠን ባለና በብልህ አስተሳሰባቸውም ው በርካቶች እንዲያፈቅሯቸው ያደረገው።
በአንድ ወቅት በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቂ ሴቶች አሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት ሩት ''ዘጠኙም ዳኞች ሴቶች ሲሆኑ በቂ ነው'' ብለው የሰጡት ምላሽ በርካቶችን አስገርሟል፤ አስደንግጧል።
''ዘጠኙም ዳኞ ወንዶች ሲሆኑ ማንም ጥያቄ አላነሳም ነበር፤ ሙሉ ሴቶች ቢሆኑ የሚለው ሃሳብ እንኳን በርካቶችን ያስደነግጣል'' በማለት ያለውን ሴቶችን አግላይ ስርአት ተችተዋል።
በአሜሪካ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን ከፍተኛ ነው።
ለምሳሌ በአሜሪካ ሕግ መሰረት በአግባቡ አልተስተናገድኩም፤ መብቴም አልተጠበቀልኝም ያለ ሰው ቅሬታውን ለፍርድ ቤት ማሰማት የሚችል ሲሆን በቂ ምላሽ አላገኘሁም ካለ ደግሞ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሄድ ይችላል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ማንም ሊሽረው የማይችለው ውሳኔ ማስተላለፍ ይችላል።
በአውሮፓውያኑ 2000 ዓ.ም. በአሜሪካ ምርጫ ተካሂዶ የፍሎሪዳ ግዛት የምርጫ ውጤት እንደገና መቆጠር አለበት ተብሎ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦለት ነበር። ፍርድ ቤቱ ግን በድጋሚ ቆጠራ አይካሄድም በማለት የወቅቱን ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽን አሸናፊ አድርጓቸው ነበር።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ለእድሜ ልክ ሲሆን የሚሾሙት ከስራቸው ሊባረሩ የሚችሉት ምናልባት ከባድ ጥፋት ከሰሩና አሜሪካ ኮንግረስ በብቃተቃቸው አላምንም ከስራቸው ይነሱ ካለ ብቻ ነው።
የሩት ባደር ጊንስበርግን ሞት ተከትሎ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የነበረው 5 ለ 4 አሰላለፍ ሊዛባ ይችላልም ተብሎ ይፈራል። ወግ አጥባቂዎቹ አምስት ዳኞች የነበሯቸው ሲሆን ተራማጅ (ሊበራል) የሚባሉት ደግሞ 4 ዳኞች ይወክሏቸው ነበር።
አሁን ግን የሩት ባደር ጊንስበርግን ሞት ተከትሎ ምናልባት ሌላ ወግ አጥባቂ ዳኛ የሚሰየም ከሆነ ተራማጆቹ ሊዋጡ ይችላሉ። ቁጥሩም ከ5 ለ4 ወደ 6 ለ3 ይቀየራል ማለት ነው።
ወጣም ወረደ ማንኛውም አይነት ሩት ባደር ጊንስበርግን የሚተካው ሰው በቀጣይ ዶናልድ ትረምፕ አልያም ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በዋይት ሀውስ ማሳለፋቸውን የመወሰን አቅም አለው።












