3.2 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡት የተሰረቁ ጥንታዊ መጻሕፍት ተገኙ

የተገኙት ጥንታዊ መጽሐፍት

የፎቶው ባለመብት, METROPOLITAN POLICE

ለንደን ውስጥ ከሚገኝ መጋዘን የተሰረቁ፣ 3.2 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ወደ 200 የሚጠጉ መጻሕፍት ሮሜንያ ውስጥ እንደተገኙ ፖሊስ ገለጸ። ከመጻሕፍቱ መካከል በጋሌሊዮና አይዛክ ኒውተን የተጻፉ ይገኙበታል።

መጻሕፍቱ ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር የተሰረቁት። ከዚያም በሮሜንያ ገጠር ውስጥ በሚገኝ አንድ መጋዘን ውስጥ ተደብቀው ተገኝተዋል።

ዘራፊዎቹ የሮሜንያ የወንጀል ቡድን አባላት መሆናቸው ተገልጿል። 13ቱ ላይም ክስ መመስረቱ ተነግሯል።

ኔሜት በምትባል የሮሜንያ ግዛት ውስጥ በተደረገ አሰሳ መጻሕፍቱ ከመጋዘን በታች ተቀብረው ነው የተገኙት።

መርማሪዎች እንዳሉት፤ መጻሕፍቱን ለማግኘት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በሮሜንያ እና በጣልያን 45 ቤቶች ላይ አሰሳ አካሂደዋል።

ከተሰረቁት መጻሕፍት ውስጥ ለማግኘት አስቸጋሪ የሆኑት የዳንቴ፣ ፍራቸስኮ ደ ጎያ እና ሌሎችም የ16ኛው እና የ17ኛው ክፍለ ዘመን ሥራዎች ይጠቀሳሉ።

መርማሪ አንዲ ዱርሀም “በጣም ውድ መጻሕፍት ናቸው። ሊተኩ አይችሉም” ብለዋል።

መጻሕፍቱ ላስ ቬጋስ የሚካሄድ ጨረታ ላይ ከመቅረባቸው በፊት ሂትሮው አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ያለ መጋዘን ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገው ነበር። ዘራፊዎቹ 12 ሜትር ጉድጓድ ቆፍረው ነበር የቀበሯቸው።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ መጻሕፍቱ ተቀብረው ስለነበር የት እንዳሉ ለማወቅ የሚረዳን የመለያ መሣሪያ (ሴንሰር) ማለፍ ችለዋል።

የሮሜንያ የወንጀል ቡድኖች ከዚህ ቀደምም ከዩናይትድ ኪንግደም የዘረፏቸውን ቁሳቁሶች ሳይታወቅባቸው ከአገር ማስወጣት ችለዋል። የተለያዩ የሟጓጓዣ አማራጮችንም እንደሚተቀሙ ተነግሯል።