በኮሮናቫይረስ የተያዘችው ስደተኛ ሄሊኮፕተር ውስጥ ልጇን ተገላገለች

በላምፔዱሳ የሚገኝ የስደተኞች ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ጣልያኗ ላምፔዱሳ ደሴት በሚገኝ እጅግ በተጨናነቀ የስደተኞች ማቆያ ውስጥ የነበረች አንዲት በኮሮናቫይረስ የተያዘች ሴት ወደተሻለ ሕክምና ስፍራ በሄሊኮፕተር እየተወሰደች ሳለ እዛው ሄሊኮፕተሩ ውስጥ ልጇን መገላገሏ ተሰምቷል።

ልጇን በሰላም የተገላገለችው እናት ምጥ ውስጥ ሳለች ነበር የኮሮረናቫይረስ ምርመራ የተደረገላት።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ወላዷ እናት በደሴቲቱ ውስጥ በሚገኝና መያዝ ከሚገባው አስር እጥፍ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ በሚገኝ ማዕከል ውስጥ ነበር የቆየችው።

ባለስልጣናት በበኩላቸው የሴትዮዋ ሁኔታ ስላሳሰባቸው በሲሲሊ ዋና ከተማ ፓሌርሞ ወደሚገኝ ሆስፒታል ለማዘዋወር መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ምንም እንኳን የሄሊኮፕተር በረራው አንድ ሰአት ያክል ብቻ የሚፈጅ የነበረ ቢሆንም ሴትዮዋ ግን ሳይታሰብ አየር ላይ እያለች ልጇን ተገላግላለች።

ስደተኛዋ ሴት ከየት አገር እንደመጣችና ሴት ይሁን ወንድ የወለደቸው ያልተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ሰአት በፓሌርሞ ሆስፒታል ከነልጇ በጥሩ ጠንነት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በሌላ በኩል 27 የሚሆኑ ተጨማሪ ስደተኞች በአነስተኛ ጀልባ ተጭነው ወደ ጣልያን ለመግባት ሲሞክሩ ባህር ላይ መንቀሳቀስ ያቃታቸው ሲሆን የድረሱልን ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው።

አንድ የንግድ መርከብም ከማልታ በደረሰኝ ጥሪ መሰረት ባደረግኩት አሰሳ በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ ስደተኞቹ ባህር ላይ እየተንገላቱ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብሏል።

ሁኔታቸውም ''እጅግ አሳሳቢ'' ነው ሲል ገልጾታል።

ጣልያን በዚህ ዓመት በርካታ ስደተኞች እየመጡ መሆኑንና ሁኔታው ከባድ እየሆነ መምጣቱን ገልጻለች።

የተባበሩት መንግሥታት ለጣልያን መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሰረትም 353 የሚሆኑ ስደተⶉች ከትናንት በስቲያ ከባህር ላይ እርዳታ እንዲደረግላቸው አንድ መርከብ መሰማራቱም ተገልጿል።

በዚህ ዓመት ብቻ 19 ሺ 400 የሚሆኑ ስደተኞች ወደ ጣልያን የውሀ ክልል የገቡ ሲሆን ባለፈው ዓመት ግን መግባት የቻሉት 5 ሺ 200 የሚሆኑት ብቻ እንደነበር ሩዌይተርስ ዘግቧል። ይህም በዚህ ዓመት ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ጭማሪ መኖሩን ያሳያል ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት እንደሚለው በፈረንጆቹ 2020 ብቻ 40 ሺ የሚሆኑ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ባህር አቋርጠው የገቡ ሲሆን 443 ሰዎች ደግሞ በባህር ጉዞ ላይ ሳሉ ሕይወታቸው አልፏል።

ኮሮና
Banner