ናይጄሪያዊው ስደተኛ ሚሊዮን ዶላሮችን ሲያጭበረብር ነበር ተብሏል

የፎቶው ባለመብት, NSW POLICE
የአውስትራሊያ ፖሊስ ሲድኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ሆኖ ሚሊዮን ዶላር እያጭበረበ ነው ያለውን ናይጄሪያዊ በቁጥጥር ሥር አውሏል።
የ43 ዓመቱ ናይጄሪያዊ የኢሜይል ማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም በርካቶች ገንዘብ እንዲልኩለት አድርጓል በሚል ነው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው።
ሌሎች ሦስት አጋሮቹም በፖሊስ እጅ ሥር እንዳሉ ታውቋል።
ግለሰቦቹ ታማኝ ኩባንያ በመምሰል የኢሜይል መልዕክት በመላክ ወደ 3 ሚሊዮን ዶላር ገደማ አጭበርብረዋል ተብሏል።
ገንዘቡ ናይጄሪያ ውስጥ አድራሻው ወዳልታወቀ ተቀባይ እንደተላከ እና የመመለሱ ነገር አስቸጋሪ እንደሆነም እየተነገረ ነው።
ግለሰቦቹ 16 ስልኮችና እና 17 ሲም ካርዶች በመጠቀም ነው ከስደተኞች ጣቢያ የማጭበርበር ሂደታቸውን ሲያጧጡፉት የነበረው።
አንድ የ20 ዓመት ግለሰብ እና ሌሎች ሁለት ሴቶች ናቸው በአጋርነት በመሥራት የተጠረጠሩት።
የአውስትራሊያ ፖሊስ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ገንዘቡን ለማስመለስ እንደሚጥር አስታውቋል።
ኩባንያዎች በስሞቻቸው የሚፈፀሙ መሰል ማጭበርበሪያ ዘዴዎችን እንዲቆጣጠሩም መክረዋል።
በከፍተኛ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ለ600 ገደማ ስደተኞች ዞሮ መግቢያቸው ነው።
ከ60 ሃገራት ያክል የመጡ ግለሰቦች በመጠለያ ሥፍራው እንደሚገኙ ባለፈው ታህሳስ ተዘግቦ ነበር።












