ካናዳውያን፡ አሜሪካውያን ወደ ሃገራችን እንዳትመጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስና የካናዳ ድንበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ውጥረት ሰፍኖታል። ምክንያቱ ቢሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ።
ካናዳውያን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግብሩ የጠፋባቸው አሜሪካውያን ቫይረሱን ይዘው ወደ ሃገራቸው እንዲመጡባቸው አይፈልጉም።
ፒች አርክ እየተባለ የሚጠራው በአሜሪካዋ ዋሺንግተን ግዛትና በካናዳዋ ብሪቲሽ ኮለምቢያ መሃል የሚገኘው ባለ 20 ሜትሩ ሽንጣም ኬላ የሁለቱ ሃገራት ውጥረት ከምን እንደደረሰ ማሳያ ነው።
"እኚህ በሮች መቼም ቢሆን አይዘጉ" የሚል ፅሑፍ የሰፈረበት ይህ ኬላ ኮሮናቫይረስ ይመጣብኛል ብሎ ያሰበ አይመስልም።
አሜሪካና ካናዳ 8 ሺህ 891 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ነፃ የሆነ ድንበር ይጋራሉ።
ለ100 ዓመታት ያክል ሕጋዊ [አንዳንዴም ሕግ ያልበገራቸው] ሰዎች ሲያሻቸው ወደ ካናዳ ይወጣሉ አሊያም ወደ አሜሪካ ይወርዳሉ።
አሁን ግን ይህ ኬላ ተዘግቷል።
ድንበሩ የተዘጋው ባለፈው መጋቢት ነው። በሁለቱ ሃገራት ስምምነት መሰረት። ስምምነቱ ብዙ ጊዜ ሲራዘም ቆይቶ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች እስኪ እስያዝነው ወር መጨረሻ ድረስ እንየው ቢሉም ብዙዎች ድንበሩ ይከፈታል የሚል ተስፋ የላቸውም።
ምንም እንኳ የድንበሩ መዘጋት በአቅራቢው ለሚኖሩ ሚሊዮኖች የገቢ ባልቦላቸው እንዲዘጋ ቢያደርግም ካናዳውያን ግን ኬላው እንደተዘጋ ቢቆይ ደስታቸው ነው።
ሐምሌ ላይ ጥናት የሠራ አንድ ድርጅት ከ10 ካናዳውያን ስምንቱ ድንበሩ ይዘጋ፤ አሜሪካውያንም እንደው እስከ ዓመቱ መጨረሻ ባይመጡብን ይላሉ ይላል።
ወረርሽኙ አሜሪካን ማጥለቅለቁን ሲቀጥል
በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ድንበር ማቋረጥ የማይታሰብ ነው። ሸቀጥ ይዘው ድንበሩን ደጋግመው የሚጎበኙ የጭነት መኪናዎች አስፈላጊ ከሚባሉ ውስጥ በመመደባቸው እንደልባቸው ይንቀሳቀሳሉ።
የአሜሪካ ታርጋ የለጠፉ የጭነት መኪናዎች በካናዳውያን የሚደርስብን መገለል አልበቃ ብሎ መኪናችን ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው ሲሉ ያማርራሉ።
ይህ ሁኔታ ስጋት የጣለባቸው የካናዳዋ ብሪቲሽ ኮለምቢያ ግዛት አስተዳዳሪ ጆን ሆርጋን የአሜሪካ ታርጋ ለጥፈው የሚንቀሳቀሱ ካናዳውያን የግል መኪናቸውን ቤት አስቀምጠው በባስ አሊያም በብስክሌት እንዲንቀሳቀሱ መክረዋል።
ድንበሩ ዙሪያ ያለው ጥበቃ ጠበቅ ማለቱ ለወትሮው በቀላሉ ያልፉ የነበሩ አጭበርባሪዎችን አስጨንቋል። ከጥቂት ቀናት በፊት እንኳ የተሰረቀ መኪና ይዞ ድንበር ሊያቋርጥ የነበረን ግለሰብ ፖሊስ ለሁለት ሰዓታት ካሳደደው በኋላ ይዞታል።
ምንም እንኳ የገንዘብ ቅጣቱ ተግባራዊ መደረግ አይጀምር እንጂ ኬላው ሕግ የጣሰ ሰው ቢያንስ 750 ሺህ የካናዳ ዶላር [566 ሺህ የአሜሪካ ዶላር] ይቀጣ ተብሏል። አሊያም የስድስት ወር እሥር ይጠብቀዋል።
ይህ ቅጣት ታድያ አስበውና አቅደው ጥፋት ለፈፀሙ ብቻ አይደለም። የአሜሪካና ካናዳ ድንበርን ተሳስተው እንኳ ኳቋረጡ ቅጣቱ አይቀርሎትም።
በቅድመ ኮሮና ወቅት ቢያንስ 3 መቶ ሺህ ሰዎች በየቀኑ የአሜሪና ካናዳ ድንበርን ያቋርጡ ነበር።
ነገር ግን ከመጋቢት በኋላ ነገሮች እንዳይሆኑ ሆነዋል። የድንበሩ መዘጋት ለአካባቢው ከተማዎች የምጣኔ ሃብት ኪሳራ ቢሆንም ካናዳ ድንበሯን ለአሜሪካ ክፍር ብታደርግ ኖሮ የበለጠ ዋጋ ልትከፍል ትችል እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ።
አሜሪካ ወረርሽኙ እንደ አዲስ ጎምርቶባታል። በቀን እስከ 40 ሺህ ድረስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እየተረጋገጠ ነው። ካናዳ ደግሞ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።













